ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፤መስከረም 26/ 2019 (ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት አሃድ በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት፤ ኮሚሽኑ ከህዳር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ አድርጓል።

መንግስት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ስራዎችን ቢያከናውንም ህገ ወጡ የሕወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምንት የፈረመውን ትጥቅ የማስፈታት ስምምነት በማፍረስ ወደ ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት ፈቃደኛ የነበሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዳይወስዱ ሲያደናቅፍ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ወጣቶችን አስገድዶ በማፈስ ለሌላ ጦርነት ሲያዘጋጅ እንደነበርም ነው የገለጹት።
 
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ መንግስት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሩ እንዳይቋረጥ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት መንግስት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም በትግራይ ክልል የሰላም መንገድን መርጠው ወደ ፌዴራል መንግስት የሚመጡ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
 
በመሆኑም በትግራይ ክልል የቀደሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት አሀድ እያስረከቡ ወደ የተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚህም መንግስት በርካታ ሃብት መድቦ ዜጎችን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን፤ በግጭት ውስጥ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን የሚያከናውን ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም