በትውልድ ቅብብሎሽ የፀናች ሀገር - ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
በትውልድ ቅብብሎሽ የፀናች ሀገር - ኢትዮጵያ
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ኢትዮጵያ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርባትን ጥቃት በጽናት መመከት፣ በጥበብ ማለፍና ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር ታውቅበታለች። ባለፉት ስምንት ዓመታት በመደመር መንግሥት ዕሳቤ እየተመራች፣ ከውጭና ከውስጥ የተቃጣባትን ትንኮሳ ተቋቁማ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ትገኛለች። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም ገንብታ ለቀጣናው የኃይል ምንጭ እንዲሆን አድርጋለች።
ለዚህም ነው በመውጣትና በመውረድ ታሪክ ውስጥ ጽኑ ሀገር ሆና የዘለቀችው። ጸንታ ቆማለች፤ ወደፊትም ጸንታ ትቀጥላለች። የሕዝቦቿ ሕብረት፣ የባህል መሠረት እና የሀገር ፍቅር የጽናቷ ዋስትናዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤት ናት ሲባል ቁጥር ብቻ አይደለም፤ ዕልፍ የታሪክ ውጣ ውረድን አይታ፣ በብዙ ተፈትና በብዙ ድል ታጅባ እንጂ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ወዲያ በውጭ ጠላት፣ ወዲህ ደግሞ በውስጥ ባንዳ የደረሰባትን ፈተና ለማለፍ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ገብረዋል፤ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወይም ደግሞ ሕዝብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ይበጀኛል ያለውን በነፃ ፈቃድ የመረጠበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ የታሪክ አንጓዎች ናቸው።
ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ሌሎችም ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የኢትዮጵያ ግማዶች፣ የማንነቷ ሕብረ ቀለማት፣ የታሪኳ ነጸብራቆችና የመኖሯ ዋስትናዎች ሆነው በድርሳናት ውስጥ ይከተባሉ። ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ርዕይ ሲባል የዚህ ድምር ውጤት ነው።
ሁሌም ግጭትና ቀውስ በማያጣው የአፍሪካ ቀንድ በርካታ የውጭ ኃይሎች ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅና ኃያልነታቸውን ለማሳየት ይራኮቱበታል። የቀጣናውን ሀገራት ከጎናቸው ለማሰለፍ የሚያደርጉት ሽኩቻም በግልጽ የሚታይ ነው። ለግባቸው መሳካት የቀጣናውን ሀገራት ያጋጫሉ፤ በውስጥ ጉዳያቸውም ጣልቃ እስከመግባት ይደርሳሉ።
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካን ጂኦ-ፖለቲካ መበየን የሚያስችል የሕዝብ ቁጥር፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቅምና ታሪክ ያላት ጽኑ ሀገር ናት። ይህንን ደማቅ ታሪኳን ለማስቀጠል በምታደርገው ጥረት ጠላትም ወዳጅም በዙሪያዋ ያንዣብባሉ።
ኢትዮጵያ ጽኑ ሀገር ናት ሲባል የውጭ ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎችን መመከት ብቻ አይደለም፤ በጥቁሮች አይሞከርም የተባለውንና ሕልም የሚመስለውን የዓድዋን ድል የተቀዳጀች፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆኗን ጭምር እንጂ። አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ በር የከፈተች፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት የጣለች፣ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዳግማዊ ዓድዋን በተደጋጋሚ ዕውን ያደረገች የመቻልና የፅናት ተምሳሌት ናት። በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ሁለተኛው ወረራ ወቅት ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችንና መርዛማ ጋዞችን በጦርና በጎራዴ በመመከት "ሀገሬን ለሰው አልሰጥም" በሚል ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩ የብርቱ አርበኞች ምድር ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!" ሲሉም እንዲሁ በከንቱ አይደለም፤ ለሉዓላዊነቷ፣ ለግዛት አንድነቷና ለብሔራዊ ጥቅሟ ልጆቿ የከፈሉትን በማስታወስ፣ የሚከፍሉትንም በማሰብ ነው፤ ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር ታውቅበታለች።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና የሕዝብ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ተመካካሪዎች ጋር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር የኢትዮጵያን የታሪክ ስብራት መጠገን የሚያስችል ውጤት ማስመዝገብም ተችሏል። በጠንካራ ዲፕሎማሲ የብሪክስ (BRICS) አባላትን ተቀላቅላለች፤ በዓለም አቀፍ፣ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መድረኮች ተደማጭነቷና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ ከፍ ብሏል።
ኢትዮጵያ የልማት አርበኛ ናት። ባለፉት አምስት ዓመታት በተቀየሱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና የልማት ስልቶች ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል።
ቱሪዝም ከሞተበት ተነስቶ ነፍስ ዘርቷል፤ የኢትዮጵያ ዕምቅ የቱሪዝም ሀብት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል። በማዕድን ዘርፍ ወርቅን ከኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እጅ በማውጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ተደርጓል። ግብርና የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ ለውጥ አምጥቷል፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት ተገኝቷል፤ ከውጭ ስንዴ ማስገባት ለኢትዮጵያ ታሪክ ሆኗል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ቀውሶች እና ጦርነቶች የሚፈጥሩትን ጫናዎች በመቋቋም ድል በማስመዝገብ ጽኑ ሀገር መሆኗን አስመስክራለች።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት አብረው በመኖር የገነቡት የመቻቻል፣ የጋብቻ፣ የንግድ እና የባህል ትስስር የጥንካሬዋ ምንጮች ናቸው። በችግር ጊዜ እርስ በእርስ የሚረዳዱበት ባህላዊ ሥርዓቶች አሏቸው። እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቆምም ገንቢ ሚና ተወጥቷል። የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነት በመደመር ዕሳቤ እያበበና እየጎመራ መጥቷል፤ ነገም ይቀጥላል።