የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽናት ውጤት ነው- አባዱላ ገመዳ - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽናት ውጤት ነው- አባዱላ ገመዳ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጽናት ውጤት ነው ሲሉ የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ተናገሩ።
7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ትናንት መሰየሙ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ብዙ ትርጉም ያለውና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል እያደገ መምጣቱን በተግባር ያሳየ መሆኑን አስረድተዋል።
54 ሚሊዮን ዜጎች በብዙ ውዥንብሮች፣ ዛቻዎችና ተግዳሮቶች መካከል አልፈው ድምጻቸውን በመስጠት ለዲሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ነው የተናገሩት።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፤ የመደመር መንግስት ባለፉት ጊዜያት መሬት ላይ የሚታዩ በርካታ ተጨባጭ የልማት ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በከፍተኛ የልማት ለውጥ ውስጥ ሆና ማካሄዷን አስታውሰው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን ልማት የማይፈልጉ ኃይሎች ምርጫውን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ዘመቻ ሲያከናውኑ እንደነበር ተናግረዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና በማበርከት የመደመር መንግሥት እንዲመሠረት ማድረጉንም ነው የተናገሩት።
ይህም የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ህዝብ የጽናት ውጤት መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ በጥንካሬ የቀጠለችው ሊበትኗት እና ሊገፏት የሚፈልጉ ጠላቶች ስላልነበሩ ሳይሆን በህዝቦቿ ጽናት መሆኑንም አብራርተዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ አገርን ለማፍረስ ከሚሰራ ኃይል ጋር መቼውም እንደማይተባበር በምርጫው በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
የመደመር መንግስት ምስረታም ኢትዮጵያ ትልቅ አገር መሆኗን በተግባር እየገለጠች እንደምትቀጥል ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል።
አዲሱ መንግስትም የተጀመረውን የልማትና የዘላቂ ሰላም ጉዞን ማፋጠን፣ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እና የኢትዮጵያን ተጽእኖ ፈጣሪነት ማጉላት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።