ቀጥታ፡

በቅብብሎሽ የሚተወነው ጥበብ

መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ በቅብብሎሽ የሚተወነው ጥበብ

የጥጥ ምርት ለኢትዮጵያዊያን የሽመና ግብአት የባህል አልባሳት ምንጭ ብቻ አይደለም፤ ታሪክን፣ ባህልን፣ የኑሮ ዘይቤንና የማንነት መገለጫን ጥበብና መጠበብን ያየዘ የባህል አምባሳደር ነው። በኢትዮጵያ የሽመና ውበቶችና የእጅ ሥራ ውጤቶች ከጥጥ ጋር የተሳሰረ የረጅም ጊዜ ትስስር ያለቸው መሆኑም ይታወቃል። 

ከጥጥ የሚሰሩ የሽመና ውጤቶች (የባህል አልባሳት) በውብ ድዛይን ተሰርተው የውበት አድማቂ፣ ለአይን ማራኪ እና የኢትዮጵያዊያን የአደባባይ መገለጫ እየሆኑ መጥተዋል። 

የባህል ልብስ በባህላዊ ዝግጅቶችና በሃይማኖታዊ በዓላት ብቻ የሚለበስ ልብስ ከመሆን እየወጣ ወደ ዘመናዊ ፋሽን እየተቀላቀለም ይገኛል። ከባህላዊ መገለጫነቱም ባለፈ የብዙዎች የገቢ ምንጭ ሆኖ እየኖሩበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ንጉስ - ጥጥ በሽመና ጥበብ የኢትዮጵያ የባህል መገለጫ፣ የቆነጃጅቶች ማጌጫ ሆኗል ማለት ይቻላል። እነዚያ ጠቢባን ጥጥን ወደ ክር፣ ክሩን ወደ ጨርቅ፣ ጨርቁንም ወደ ልብስ በመቀየር ጥበብ ያደርጉታል፤ ለዚህም ነው አንዳንዶች የጥጥ ምርትን ለኢትዮጵያዊያን የጥበብ ንጉስ እያሉ የሚጠሩት።

በኢትዮጵያ ጥጥ አንድ ሰው ብቻ የሚያመርተው ወይም የሚያቀናብረው ምርት አይደለም። ከአርሶ አደሩ ጀምሮ አምራች፣ ፈታይ፣ ሸማኔ፣ የስፌት ባለሙያና የፋሽን ዲዛይነር በቅብብሎሽ የሚተውኑት ጥበብ ነው። ከዚህም ባሻገር በግብርና፣ በጨርቃጨርቅ፣ በአልባሳትና በንግድ ዘርፎች የሚፈጥረው የእሴት ሰንሰለት ሰፊ ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ጥጥን በበቂ መጠንና በጥራት በማምረት ከማሳ እስከ አልባሳት ያለውን እሴት በደንብ አስተሳስሮ መስራት ከተቻለ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ማድረግ ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዲዛይነሮች የባህላዊ ሸማን ጥለት፣ የእጅ ሽመና ጥበብና የአካባቢያዊ ባህል መገለጫዎችን ከዘመናዊ የልብስ ዲዛይን ጋር በማዋሃድ አዳዲስ የፋሽን ምርቶችን እየፈጠሩ ይገኛሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃም የጥጥ ምርት ለሚሊዮኖች አምራቾችና ቤተሰቦች የኑሮ መሠረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የዓለም የምግብና የእርሻ  ድርጅት (FAO) መረጃ እንደሚያመለክተው ጥጥ በተለይ በገጠር ለሚኖሩ አነስተኛ አምራቾችና ሠራተኞች የስራ እድልና አይነተኛ የገቢ ምንጭ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥጥ ምርት 80 በመቶው ለአልባሳት የሚውል መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚህም መሰረት የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 በየዓመቱ የዓለም የጥጥ ቀን ሆኖ እንዲከበር በወሰነው መሰረት በመከበር ላይ ይገኛል። በነገው እለት የዓለም የጥጥ ቀን የሚከበረውም በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በሥራ ፈጠራና በድህነት ቅነሳ ረገድ ያለውን አስተዋጽኦ መሰረት በማድረግ ነው። የዘንድሮው የዓለም የጥጥ ቀንም  «ጥጥን ከገቢ ምንጭ፤ በተለይም ለአርሶ አደሮች የኢኮኖሚ እድሎችን ከመፍጠርና የዘላቂ ልማት መሰረት” አድርጎ ማስቀጠል በሚል መርህ በዩዝቤኪስታን ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም