ኢትዮጵያ ከእመርታ ወደ ልዕልና - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከእመርታ ወደ ልዕልና
ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ውስብስብ ፈተናዎች በፅናትና በስክነት በመሻገር፣አሁን ላይ አዲስ ብሔራዊ የዕድገት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ሀገሪቱ ቀደም ሲል የነበረውን “አይቻልም” የሚል የተስፋ መቁረጥ ትርክትን በመስበር ሁለንተናዊ የማንሰራራትና የእምርታ ጉዞ እያደረገች ትገኛለች።ይህ ጉዞ የዜጎችን አስተሳሰብና የሥራ ባህል ከመቀየር ባለፈ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች የሚመጥናትን ታሪካዊ ከፍታ ለመያዝ ወደ ላቀ የሐሳብና የልማት ልዕልና የምታደርገውን ሽግግር የሚያመላክት ነው።ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለዚህ የልዕልና ምዕራፍ ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለ ማንም የውጭ ዕርዳታ፣በሀገር ውስጥ ዕውቀትና ጥረት መገንባቱ የኢኮኖሚና የኃይል ሉዓላዊነትን ከማረጋገጡም በላይ ሀገሪቷን የቀጣናው የብርሃን ተስፋ አድርጓታል።
በግብርናው ዘርፍ በስንዴ ልማት ከውጭ ገዥነት ወደ ላኪነት መሸጋገር መቻሉና የሌማት ትሩፋት ለተሟላ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ እየተወጣ ያለው ወሳኝ ሚና፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ የሆነው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክትና በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የሀገሪቱ ገጽታ በአዲስ መልክ መታደሱ ከታዩት እመርታዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ይህንን የሀገር ውስጥ አቅምና የተመዘገቡ ውጤቶችን አስመልክቶ፣ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ባደረጉት ንግግር የሀገሪቱን ታላቅነት አረጋግጠዋል። ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ ላለፉት ዓመታት የተከናወኑት የማክሮ-ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው ናቸው።
የፖለቲካ ልምምዱን ከነፍጥ አዙሪት በማውጣት በሰላም፣በውይይትና በመደማመጥ ላይ የተመሠረተ የሀሳብ ልዕልና የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት ቅድሚያ መሰጠቱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፣የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያሸጋገራት መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የተገኙ ስኬቶችን በማጽናት ይህንን ከእምርታ ወደ ልዕልና የሚደረገውን ሽግግር ይበልጥ ለማፋጠን በርካታ ብሔራዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። በዚህም በ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት የ10.1 በመቶ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብና የዋጋ ግሽበትን ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ ጥብቅ የፊስካል ሥርዓት ይተገበራል።
ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን 65 በመቶ፣የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን 85 በመቶ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች የሚተገበረውን የምገባ መርሐ ግብር ሽፋን 70 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል።
የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት ውጥንን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የማሳካት እና 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP32) በብቃት የማስተናገድ ራዕይ ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት የምታረጋግጠውን የልዕልና ከፍታ የሚያሳዩ የጉዞ ምዕራፎች ናቸው።