ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት የያዛቸው የልማት እቅዶች ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሸጋግሩ ናቸው- የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች 

ቦንጋ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦የመደመር መንግስት በቀጣይ ለመተግበር የያዛቸው ዕቅዶች ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሸጋግሩ መሆኑን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገልጹ።

በቀጣይ የሚተገበሩ ዕቅዶች ከዳር እንዲደርሱ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ  ተናግረዋል።

የመደመር መንግስት በትላንትናው እለት በይፋ ተመስርቶ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቃለመሀላ ከፈፀሙ በኋላ የመንግስታቸውን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በዲፕሎማሲው መስኮች  ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ንግግር አድርገዋል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች፤ የመደመር መንግስት ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ብልፅግና ያረጋግጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡


 

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሉጌታ ከፍያለው እና አቶ አዳሙ እሸቱ እንደተናገሩት የመደመር መንግስት እንደሀገር የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ከዳር በማድረስ  ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሸጋግራት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ያነሷቸው ጉዳዮች ኢትዮጵያዊያን የሚጠብቁትና የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተለይም የባህር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት ነዋሪዎቹ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር መልሳ እንድታገኝ የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የገጠርና የከተማ ልማቶችን ለማሳለጥ መንግስት ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ከዳር እንዲደርሱ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

አዲስ የተመሰረተው መንግስት የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ አተኩሮ እንዲሰራም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።


 

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዳግም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው በሀገሪቱ ሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የእድገት ጉዞዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አየለች ወልደሚካኤል እና ወይዘሮ አለምነሽ አደቶ ናቸው።

በሚቀጥሉት ዓመታት መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ፣ ሰላምን የማጽናት እና ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችን የማስፋት ስራዎች ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎችን ከማስቀጠል ባሻገር ሙስናን የመከላከል እና መልካም አስተዳደርን የማስፍን እንዲሁም የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራዎችን መንግስት አበክሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ለዚህም ስኬታማነት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና ድጋፍ አስፈላጊ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም