ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቷል

ድሬዳዋ፣ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት መስጠቱን የአስተዳደሩ ከንቲባ አብዱላሂ አደን አስታወቁ።

የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የውሃ፣ የመንገድ እና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

ከንቲባ አብዱላሂ አደን በወቅቱ እንደገለፁት፤ አስተዳደሩ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቷል።

ዘላቂ ሰላምና ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለዚህም ቀደም ብለው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ ብለዋል።

ሰው ተኮር የልማት እና የመልካም አስተዳደር ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው በጀት እና ጊዜ ለማጠናቀቅም ነዋሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት እንደሚሰራ አንስተዋል።

በተለይም በገጠር እና በከተማ የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

የካቢኔ አባላቱም የቢሮ የስራ እንቅስቃሴዎችን፣ የወረዳ እና የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ እና የህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፈታትን ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም