የተጀመረው ሁለንተናዊ እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመደመር መንግስት ጎን በመሰለፍ የድርሻችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረው ሁለንተናዊ እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመደመር መንግስት ጎን በመሰለፍ የድርሻችንን እንወጣለን
ደሴ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦በመላው ሀገሪቱ የተጀመረው ሁለንተናዊ እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመደመር መንግስት ጎን በመሰለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪ ሼህ መሐመድ ሰይድ፤ በዘንድሮው ምርጫ ድምፃቸውን የሰጡት የመደመር መንግሥት ሰላምን ለማፅናትና ልማትን ለማጠናከር ሙሉ እምነት ስላላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ገንብቶ በማጠናቀቅ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከአዲሱ የመደመር መንግሥት ጎን እንደሚቆሙም ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት፣ የባሕር በር፣ ሰው ተኮር ልማቶችና ሌሎች ኢንሼቲቮችን አጠናክሮ በማስቀጠል የሀገሪቱን እድገት እውን ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራትም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አቶ ይመር አሊ በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት በየመስኩ ያስመዘገበው የልማት ውጤትና አፈጻጸም ዳግም ድምፃችንን እንድንሰጠው አድርጎናል ብለዋል።
በደሴ ከተማ በኮሪደር ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በከተማ ግብርናና በሌሎች የልማት ሥራዎች እምርታ እየተመዘገበ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በተመሠረተው ምክር ቤት ቀርበው ባስቀመጡት ቀጣይ አቅጣጫ መሠረት የሚከናወኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራት እንዲሳኩ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት፣ ሙስናን ለመከላከልና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ አሠራርን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት የሚደገፍ ነው ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሥርካለም አበበ ናቸው።
ለዘላቂ ሰላምና ልማት፣ የወል ትርክትንና ሌሎችንም እሴቶች በማጎልበት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩም ጠቁመዋል።
በተለይም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሰላምን ለማፅናትና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መንግሥት እየተከተለው ያለውን አቅጣጫ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።