ቀጥታ፡

በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኘው ስኬት በበጋውም ተጠናክሮ ይቀጥላል

ገንዳውኃ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገኘውን ስኬት በበጋ ወራትም በማስቀጠል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ይጠናከራል ሲል የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። 

በምዕራብ ጎንደር ዞን የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠናቀቂያና የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ተካሂዷል።

 የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘላለም አረጋ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ መጥቷል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር እያጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፣ አገልግሎቱ የወጣቶችና የሴቶች የልማት ተሳትፎ እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

በከልሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አስተዋጽኦ ላደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበው፣ የበጎ ፍቃድ ተግባራት በበጋ ወቅትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ በበኩላቸው ​እንዳሉት፤ በጎነት ጊዜን፣ ቦታን፣ ብሔርን እና ቀለምን የማይለይ የማህበረሰባችን መገለጫ እሴት ነው።


 

በዚህም በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶችን በበጋ ወራትም ለማስቀጠል አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግሥት እማኘው በበኩላቸው፤ በክረምቱ ከ240 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዞኑ ነዋሪዎች ከ434 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል።

በክረምቱ በበጎ ፈቃደኞች ከተከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል 240 የአቅመ ደካማ ቤቶችን መጠገንና በአዲስ የመገንባት፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የመትከል እንዲሁም 521 ዩኒት ደም የመለገስና ሌሎች የልማት ሥራዎችን የማከናወን ሥራዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

የተገኘውን ተሞክሮ በማስቀጠል በበጋ ወራትም ከ120 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ182 ሺህ በላይ ዜጎችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።


 

የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪ ወጣት አድኖ በበኩሉ፤  በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የተለያዩ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን በበጋው ወራትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም