ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል

ዲላ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነቱን ማሳደግ መቻሉን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለጸ። 

በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ በኩታ ገጠም አሠራር የተከናወነ የቡና ልማትና የምርት ዝግጅት የመስክ ምልከታ ተካሄደ።


 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳሉት፣ የልማቱ ዋና ዓላማ ያረጁ የቡና ዝርያዎችን በተሻሻሉ ተክሎች በመተካት የአርሶ አደሮችን የዘርፉ ተጠቃሚነት ማሳደግ ነው።

የኩታ ገጠም አሠራሩ በሄክታር ከ19 ኩንታል በላይ ምርት ማስገኘት መቻሉን አቶ አማኑኤል ጠቅሰው፣ ይህም ከክልሉ አማካይ የምርት መጠን ከእጥፍ በላይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም የኩታ ገጠም የቡና ልማትን በማስፋት በሁሉም አካባቢዎች ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ እንደሚገኝና የመስክ ምልከታውም የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።

በዞኑ ከ2 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም አሠራር በቡና ልማት መሸፈኑን የገለጹት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ የቡናና ቅመማ ቅመም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማኑኤል ወርቁ ናቸው።


 

በዞኑ ያረጁ የቡና ተክሎችን በመንቀል በተሻሻሉ ዝርያዎች በኩታ ገጠም የማልማቱ ሥራ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የጥምር ግብርና ልማትን እያጠናከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተያዘው የምርት ዘመንም ከ38 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የምርት ማሰባሰብና የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በወናጎ ወረዳ ቱማታ ጭራቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወጋየሁ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ቡናን በኩታ ገጠም ማልማታቸው የምርት መጠንና ጥራትን ከማሻሻል ባሻገር የሥራ ባህላቸውን እንደቀየረው ጠቅሰዋል።


 

የኩታ ገጠም ልማቱ ዘመናዊ አሠራርን ይዞ በመምጣቱ የመጀመሪያ ምርታቸውን በሁለት ዓመት ውስጥ ማግኘት መቻላቸውን ያነሱት አርሶ አደር ወጋየሁ፣ ይህም ከዚህ ቀደም አምስት ዓመታት ይወስድ የነበረውን ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

ልማቱ ከቡና እርሻ ባሻገር ለዶሮና ንብ እርባታ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም አክለው ገልጸዋል።

በመስክ ምልከታው የክልሉ እና ከጎፋ ዞን የመጡ የዘርፉ አመራሮች፣ አምራቾችና አቅራቢዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም