የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ለዘላቂ ሀገር ግንባታ እንዲውሉ ይደረጋል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ለዘላቂ ሀገር ግንባታ እንዲውሉ ይደረጋል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦችን መሬት በማውረድ ለዘላቂ ሀገር ግንባታ እንዲውሉ ይደረጋል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
የሙስናን አረንቋ የማድረቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።
በዚህም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎቻቸውን በመሰየም ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፤ ሀገራዊ ስትራቴጂክ ግቦችን ለማሳካት የሐሳብ ጥልቀት፣ የእውቀት ደርዝና የሥራ ተነሳሽነት ወሳኝ ኃይሎች ናቸው ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያን በጸና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በማስቀጠል ዜጎች ለሀገር ብልፅግና በጋራ መንፈስ እንዲተጉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የነፍጥ አዙሪትንና የአመጽ የፖለቲካ ውርስ በዘላቂነት ለማስቀረት የፖለቲካ ልምምዳችን በሰላም፣ በንግግርና በመደማመጥ ላይ እንዲመሠረት መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
የሀገራዊ የምክክር ምክረ ሐሳቦችና የውይይት ውጤቶች ለፖለቲካ ልምምድና ለዘላቂ ሀገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ ተገንዘቦ በዳበሩ ሀገራዊ ሐሳቦች ወደ መሬት እንዲወርዱ ይደረጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካና ማኅበራዊ ንቃት ከፍ በማድረግ ልዩነቶችን በማጥበብ ሰላምና ዕድገት የሰፈነባት ተምሳሌታዊ ሀገር የሚገነባ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
ተቋማትን በቁጥጥር ሥርዓት በማጠናከርና ሠራተኞችን በሥነ ምግባር በማብቃት የሙስናን አረንቋ የማድረቅ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ፣ በኮሪደር ልማት እና በግብርና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎችን በማስፋት የሕዝብን ተሳትፎ ማዕከል ያደረገ የኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴ እንደሚረጋገጥም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጉዞ አቅጣጫ ሁለንተናዊ ኃይልን በማጠናከር በቴክኖሎጂ ራስን መቻልን፣ መከላከልን ማሳደግና የውስጥ ጥንካሬን መገንባት መሆኑንም አክለዋል።
ጠንካራ የተቋም ግንባታ፣ሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት እና ሁለንተናዊ ኃይልን ማጠናከር የሀገሪቱን የነገ ዕድገት እውን የሚያደርጉ አንጡራ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።