ቀጥታ፡

የተጀመሩ የልማት ኢኒሼቲቮችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሥራ ይጠናከራል

ሮቤ፣መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ የተጀመሩ የልማት ኢኒሼቲቮችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሥራ እንደሚጠናከር የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ኢድሪስ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በዞኑ አጋርፋ ወረዳ በመገኘት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን በመስክ ተመለከቱ።

አቶ አህመድ ከጉብኝቱ በኋላ ስለ አዲሱ አደረጃጀት፣ በመሬት ላይ ስለሚታዩ ነባራዊ ሁኔታዎችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ለኢዜአ አስተያየት ሰጥተዋል።

አስተዳዳሪው በወቅቱ በሰጡት አስተያየት፣ የክልሉ መንግሥት የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል ተግባራዊ ያደረጋቸው የልማት ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በኩታ ገጠም አሠራር ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የግብርና ሥራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነትና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአርሶ አደሩ ምርት ላይ ተጨማሪ እሴት በመፍጠር በተደራጀ መልኩ ወደ ገበያ እንዲቀርቡና አርሶ አደሩ ከምርቱ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ የሚያስችሉ የፓስታና ማካሮኒ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ የሚበረታቱና በቀጣይም ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተጀመሩትን የግብርናና ሌሎች የልማት ኢኒሼቲቮች በተሻለ መልኩ በማጠናከር የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገው የቀበሌና የወረዳ አደረጃጀት ሕዝቡ በአስተዳደር ሥርዓቱ የበለጠ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉንም አቶ አህመድ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ መልኩ ተግባራዊ የተደረገው የዞን አደረጃጀት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥና ከዚህ ቀደም የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አደረጃጀቱ ነዋሪው ከአካባቢው ሳይርቅ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በአቅራቢያው እንዲያገኝና የልማት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

በክልሉ ከዚህ ቀደም በላይኛው የአደረጃጀት እርከን አካባቢ ተከማችቶ የነበረው የውሳኔ ሰጪነት ተግባር በተጠና መልኩ በየደረጃው ወደ ተደራጁ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌዎች ተደራሽ እንዲሆን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይም የገጠርና የከተማ ትስስርን ማጠናከር፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ማፋጠንና የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ከተያዙ ቁልፍ ግቦች መካከል መሆናቸውነ አቶ አህመድ አብራርተዋል።።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም