ቀጥታ፡

አዲሱ የኦሮሚያ ክልል የዞን አደረጃጀት መልካም አስተዳደርን በዘላቂነት ለማስፈን ያስችላል

አዳማ ፤መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የዞን አደረጃጀት በየመስኩ የህዝብ ጥያቄዎችን በመመለስ መልካም አስተዳደርን በዘላቂነት ያሰፍናል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ ፤ ታላቅ ርዕይ

የአዳማ ከተማ ባህል ፍርድ ቤት ዳኛና የሀገር ሽማግሌ ጠሃ ሀምዳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የክልሉ መንግሥት ያወጣውና የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ያጸደቀው አዲሱ የዞን አደረጃጀት በሕዝብ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን የተተገበረው አዲሱ የዞኑ አደረጃጀት ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማነት በር ከፋች ነውም ብለዋል።

የመደመር መንግሥት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ይበልጥ ለማስፋፋት አደረጃጀቱ ምቹ መሆኑንም የሀገር ሽማግሌው ተናግረዋል።

በተለይ በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ውስንነቶችን አርሞ በቁርጠኝነት ለመጓዝ አዲሱ የዞን አደረጃጀት ወሳኝ መሆኑንና አስታውሰዋል።

በአደረጃጀቱ የህዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ እንደ ሀገር ሽማግሌ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል። 

ዞኖቹን እንዲያስተዳድሩ የተሰየሙ አመራሮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ በልዩ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ከሰሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህዝብ እርካታን ማረጋገጥ እንደሚችሉ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ ጥላሁን ራጎ ናቸው።


 

"አዲሱ አደረጃጀት ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝና በህዝብ ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት ስላለን ለተግባራዊነቱም ከመንግሥት ጎን እንቆማለን" ብለዋል።

በተለይ አደረጃጀቱ ለህዝብ የቅሬታ ምንጭ የነበረውን የሠላም እጦት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል መልካም አስተዳደርን እንደሚያሰፍን እምነታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መሰረተ ልማቶችን በጥራት እና ባጣረ ጊዜ እውን ለማድረግ አዲሱ የዞን አደረጃጀቱ አይነተኛ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግልም አመልክተዋል።


 

የሀገር ሽማግሌ ግርማ ሰንበቶ በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል የተዘረጋው አዲስ የአስተዳደር መዋቅር የመንግስትና ህዝብ የተደመረ አቅምን በማቀናጀት ህብረተሰቡን ያማከለ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

‎በመደመር መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየአካባቢው የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ተግባራት   መከናወናቸውን አስታውሰው፣ በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ውስንነቶችን ነቅሶ በማውጣት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለማከናውን  አዲሱ የዞን አደረጃጀት የተሻለ ምህዳር ይፈጥራል የሚል አምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። 

ከአዲሶቹ የዞን አስተዳዳሪዎች ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው በመስራት የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ማርካት ይኖርባቸዋል ሲሉም አክለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም