በመደመር መንግስት የተያዙ እቅዶችና የተነሱ ትልሞች የሀገርን እድገትና የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንግስት የተያዙ እቅዶችና የተነሱ ትልሞች የሀገርን እድገትና የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ ናቸው
ወልዲያ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ) ፡-በመደመር መንግስት የተያዙ እቅዶችና የተነሱ ትልሞች የሀገርን እድገትና የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ መሆናቸው ተመላከተ።
የመደመር መንግስት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ የተመሰረተ መሆኑን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚከናወኑ አበይት ተግባራትን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የዓለምን፣ የአፍሪካንና በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ነባራዊ ሁኔታ በመቃኘት ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባውን ዝግጁነት አንስተዋል።
በሀገር ብሄራዊ ጥቅምና አጠቃላይ የዲፕሎማሲ አቅጣጫን በተመለከተ፣ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ የግብርና ልማትና ዲጅታላይዜሽን እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ አዲስ የተመሰረተው የመደመር መንግስት የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ከትናንት መልካም የሆኑትን በመውሰድ እሴት በመጨመር በቀጣይ የተሻለች ሀገር እንገነባለን ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሃሳቦች ያልዳሰሱት ጉዳይና ያላመላከቱት የወደፊት ትልም የለም ብለዋል።
በመሆኑም በመደመር መንግስት የተያዙ እቅዶችና የተነሱ ትልሞች የሀገርን እድገትና የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ አሸናፊ ሰማሁ፤ እንደ ሀገር ባለፉት ጥቂት አመታት የተመዘገቡ ስኬቶችና ተጨባጥ ውጤቶች ለቀጣይ ብሩህ ተስፋ የሰነቁ ስለመሆናቸው አንስተዋል።
ከዚህ በመነሳት የመደመር መንግስት ቀጣይ ትኩረት ለሰላምና የህግ የበላይነት መከበር ቅድሚያ በመስጠት በሁሉም ረገድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።
በተለይም በግብርና ልማት፣ በቱሪዝም፣ በዲጅታላይዜሽንና የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን አንፃር የተመለከትናቸው ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄያችን ምላሽ እንዲያገኝ የማድረግ ጥረትም የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት የሚደረግን ማናቸውንም የባንዳነት እንቅስቃሴም አጥብቀን መታገል ይኖርብናል ነው ያሉት።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ባቡ፤ የመደመር መንግስት በፈተና ውስጥም ሆኖ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያመጣው ለውጥና ያስመዘገበው ስኬት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በጠቅላላ ምርጫው አሸናፊ በመሆን መንግስት የመሰረተው ብልጽግና ፓርቲ ሀገር የመምራት እድል ማግኘቱ እነዚህን ስኬቶች ለማስቀጠልና እድገቷን ለማረጋገጥ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት፣ የኮሪደር ልማት፣ የግብርና ልማት፣ የቱሪዝም ዘርፍና ሌሎችም የሀገር እመርታዎች መሆናቸውን አንስተው በቀጣይ ለላቀ ስኬት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
አዲሱ መንግስት በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ በአገልግሎት ዘርፍና ሌሎችም ላይ አተኩሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ገነት ሙልጌታ አዲሱ መንግስት ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የሰላም ጉዳይ መሆን እንዳለበት አንስተው፤ ለዚህም ሁላችንም ባለቤት ሆነን መስራት አለብን ብለዋል።