ቀጥታ፡

ሆስፒታሉ በመደበኛና በዘመቻ በሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 26/2019(ኢዜአ)፡-የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህሙማንን ህይወት ለመታደግ በዘመቻ  የቀዶ ህክምና  እንዲያገኙ ማድረጉን  የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብይ ፍሰሃ ገለጹ። 

ከአሜሪካ፣ ከሀንጋሪ፣ ከፖርቹጋል፣ ከስፔንና ሌሎች አገራት የተውጣጡ ሀኪሞች በዘመቻው ተሳታፊ ሆነዋል። 

"የኦፕሬሽን ኢንተርናሽናል" የበጎ ፈቃደኛ ሀኪሞች ቡድን በፈለገ ህይወት ሆስፒታል በዘመቻ ከፍተኛ የቀዶ ህክምና እየሰጠ ይገኛል።


 

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብይ ፍሰሃ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዘመቻው በተራዘመ ቀጠሮ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ህሙማንን ህይወት ለመታደግ ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ ነው። 

በዘመቻው ከአንገት በላይ፣ የጽንስና ማህፀን አጠቃላይ ቀዶ ህክምና በከፍተኛ ባለሙያዎች በነፃ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 ሆስፒታሉ ከውጭ ሀገራት ሀኪሞች ጋር በመተባበር በሚሰጠው ህክምና ህሙማን ፈጣን የቀዶ ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስትና ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር የሰውበላይ ምንአለ በበኩላቸው፤ ለሰባት ቀናት በዘመቻ በሚካሄደው የቀዶ ህክምና በተራዘመ ቀጠሮ ላይ የነበሩ ከ100 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል። 

ቡድኑ ከፍተኛ የቀዶ ህክምናውን በነጻ ከመስጠቱ ባሻገር ለሆስፒታሉ ዘመናዊ የህክምና ማሽኖችን፣ መድኃኒቶችንና ሌሎች ግብአቶችን በእርዳታ ማበርከቱን አስረድተዋል።


 

ከቡድኑ አባላት መካከል ከሀንጋሪ የመጡት ዶክተር ኖቫክ አንድራስ (Novak Andras) እንደገለጹት፤ የአንጀት፣ የፊንጢጣና ሌሎች በሽታዎች ለሚሰቃዩ ወገኖች የቀዶ ጥገና ህክምና እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘመቻው ባለቤታቸው ከፍተኛ የእንቅርት በሽታ በቀዶ ህክምና ተወግዶላቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ይርጋለም ተገኘ ናቸው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ህክምናውን ለማግኘት እንደሞከሩ አመልክተው የቀዶ ህክምናው በዘመቻ መካሄዱ ባለቤታቸው ከሕመም እንዲያገግሙ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የፈለገ ህይወት ሆስፒታል እስከ 15 ሚሊዮን ለሚጠጋ ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም