ቀጥታ፡

መስከረም የታዘባቸው ጽንፎች

ኢትዮጵያ የተግባር ሀገር ናት፤ ቃሏን የምትፈጽም። ለጎረቤቶቿ ዕድገት፣ ልማትና ደህንነት በትጋት የምትሰራ፤ በጋራ መልማትና የጋራ ብልጽግናን አሻግራ የምትመለከት ጠንካራ የተግባር ምድር።

እንግዳ ተቀባይ፣ ያላቸውን አካፍለው የሚያድሩ፣ ለጎረቤት ደራሽ ብርቱና ሩህሩህ ሕዝቦች ምድር ናት ኢትዮጵያ። ከዚህ ሕዝብ አብራክ የወጣው መንግሥት ለወገኑ አጉራሽ፣ ለጎረቤቶቹ ደራሽ መሆኑ የሚጠበቅ ነው። የመንግሥት በመደጋገፍና በመረዳዳት የጋራ ብልጽግናን የማረጋገጥ ህልምም ከዚህ ይመነጫል። ለዚህ ነው ለጋራ ልማት ሌት ተቀን የሚታትረው።

የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት ፍላጎት በብዙ የተግባር መለኪያዎች ማሳየት ይቻላል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ግዙፉን የዳመርጆግ - ደወሌ የነዳጅ ምርቶች ማሰተላለፊያ መስመር ለመገንባት በቅርቡ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። 

የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ከአንድ ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የተጣራ ነዳጅ የማጓጓዝ አቅም ይኖረዋል። ቀጣናውን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር የተሳለጠ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መስጠትም ያስችላል። ይህም የቀጣናው የትስስር ፍላጎትና የተግባር ርምጃ ማሳያ ነው። ጅቡቲን ከኢትዮጵያ ጋር በነዳጅ ዘርፍ የበለጠ የሚያስተሳስር ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንትም ጭምር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ይፋ በተደረገበት ወቅት “ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች እና ግብርና ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ለጅቡቲ ደግሞ የትራንዚት መጠንን ከፍ በማድረግ እንደ ቀጣናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ያላትን ቦታ ያጠናክራል” በማለት ገልጸውታል።


 

የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመር ደግሞ ሌላው ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትብብር ያላትን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ያሳየ ነው። ፕሮጀክቱ የምስራቅ አፍሪካን ኮሪደር የኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል ለማድረግ የሚያግዝ፣ የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሀብቶችን የሚያስተሳስር ሞተር መሆኑ ተነግሮለታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የአፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም ለማሳደግ፣ መጠነ ሰፊ እድሎችን ለመፍጠር እና በመላው ምስራቅ አፍሪካ ለላቀ ኢኮኖሚያዊና የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት መሰረት ለመጣል ትልቅ እርምጃ ነው” ብለውታል። ይሄውም ኢትዮጵያ በቀጣናው የነዳጅ አቅርቦት የንግድ ኮሪደሮችን በማልማትና በማስፋት ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ስትራቴጂያዊ አካሄድ እየተከተለች መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር የመልማትና የቀጣናውን ደህነንት የማስጠበቅ የጋራ ርዕይ ሰንቃ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትና አድናቆት ማግኘቷ እንቅልፍ የነሳቸው ሀገራትም አልጠፉም። ግብፅ ዋነኛዋ ናት፤ ኤርትራም እንደ አቅሟ። ለዚህም ነው ግብጽ ለኤርትራ ብሔራዊ ጥቅም ደንታ የሌለው፤ የዘወትር ህልሙ የኢትዮጵያን ውድቀት ቆሞ ማየት የሆነው ኢሳያስ አፈወርቂን እየጎተተች የአጀንዳዋ ማስተላለፊያ አሻንጉሊት ያደረገችው። በእርግጥ ኢሳያስ ኤርትራን የመሰለ ባለብዙ ጸጋ ሀገር ምድረ በዳ አድርጎ አንድም እንኳን አውሮፕላን ሳይኖረው በተውሶ የሚንከራተት ተላላኪ ነው። 

ግብጽ ከሰሞኑ የዘወትር አገልጋይዋን ሻዕቢያ እና ሱዳን፣ ሶማሊያ መሪዎች ወደ ካይሮ ጠርታ መክራና አስፈራርታ በቀይ ባህርና በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ የስምምነት መግለጫ የሚል ጽሁፍ አስነብባ ልካቸዋለች። የግብጽ፣ የሻዕቢያ፣ የሱዳን እና የሶማሊያ መሪዎች በአዲሲቷ አል-አለሜን (New Alamein) ባደረጉት ጉባዔ “የአል-አለሜን መግለጫ” የሚል የጋራ ስምምነትና አቋም ይፋ ማድረጋቸው በመገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል። ስምምነቱ ያነጣጠረው ጠቅለል ሲል ግብጽ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አደጋ ለመደቀን አስባ ያመነጨችውን የቅዠት ሀሳብ በጋራ አቋም መልክ ማውጣት ነው።

የቀይ ባሕር ደህንነት እና አስተዳደርን በተመለከተ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ያሉ ሀገራትን ብቻ ይመለከታል ይላል መግለጫው፤ በውኃ መስመሩ ስትራቴጂካዊ አስተዳደርና ደህንነት ላይ ዋናው ሚና እንደሚኖራቸውም አቋም ይዘዋል። ከኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት በተፃራሪ መቆማቸው ነው ነገሩ፤ የመልካዓ ምድራዊና ታሪካዊ መብቷን ለመገዳደር የታሰበም ይመስላል፤ አይሳካም እንጂ።

ሌላም አለ የናይል ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ ደረስንበት ያሉት ስምምነት። ይሄ ደግሞ የቅኝ ግዛት ውልን አቧራ አራግፎ ማስነሳት ነው፤ “ከእኛ ፈቃድ ውጭ የሚካሄድ ልማት አይኖርም” የሚል ከዕውቀትም ከእውነትም የተፋታ ሀሳብ ነው።

በተፈጥሯዊና ታሪካዊ የባህር በር መብቷ አያገባሽም ያሏትን ኢትዮጵያን ከማህጸኗ የሚወጣውን የአለም ረጅሙን የአባይ ወንዝም ንክች እንዳታደርጊ ማለታቸው ደግሞ ሌላኛው ተቃርኖ ነው።  

በቀጣናዊ ጸጥታ፣ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ዙሪያ የጋራ ውሳኔዎችን ተግባራዊነት ለመከታተልና መደበኛ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ማዕቀፍ በሚል የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ ለመግታት ታሳቢ ያደረገ የቅዠት ነጥብ መኖሩም ተስተውሏል። የቀጣናው በጥባጭ ለቀጣናው ሰላም ሲያመጣ ይታያችሁ፤ በእርግጥ ረባሽ ተማሪ የክፍሉ አለቃ ይደረጋል። 

በጥቅሉ ስብሰባው በአፍሪካ ቀንድ እና በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ባለው የጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ አራቱ ሀገራት ኢትዮጵያን ያገለለ በቀይ ባህርና በዓባይ ወንዝ ላይ የቀረበ አዲስ ቀጣናዊ የሴራ ጥምረት መመስረት ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

እዚህ ላይ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች ይነሳሉ። አንደኛው የቀይ ባህርንና የዓባይን ጉዳይ ከኢትዮጵያ ውጭ ተወያይቶ ስምምነት መድረስ ይቻላል? የሚለው ሲሆን፤ ሌላው ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት እየተጋ ያለው የትኛው ሀገር ነው? የሚለው ነው።

የመጀመሪያ ነጥብ አራቱ ሀገራት አንስተው "ስምምነት ደርሰንበታል" ያሉት ነጥብ የቀይ ባሕር አዋሳኝ ያልሆኑ ሀገሮች በቀይ ባሕር ጉዳይ ቦታ የላቸውም የሚለው ነው። በ30 ማይል ርቀት ላይ የምትገኘው፣ ታሪካዊና መልከዓ ምድራዊ መብት ያላት ኢትዮጵያ በፖለቲካ ሴራ ከራሷ ከአብራኳ በወጡ ባንዳዎች ያጣችው መሆኑ እየታወቀ “ባህሩ ላይ መብት የላትም፤ መጠጋት አትችልም የእኛ የብቻችን ነው” የሚል የግብዝ ውሳኔ ያስተላልፋሉ።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አዋሳኝ ላይ ስለማትገኝ አይመለከታትም ባሉበት አንደበታቸው፤ ለዓባይ ዋነኛ ምንጭ የሆነችውንና ለተፋሰሱ 86 በመቶ ውሃ አስተዋጽኦ የምታደርገው ኢትዮጵያን “በዓባይ ላይ እኛን ሳታማክር ምንም ማድረግ አትችልም” የሚል አስቂኝ ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ይህ ዓለም አቀፍ ህግን ያልተከተለ፣ የሞራል ውድቀት፣ የአንድ ወገን ጥቅምን ብቻ የሚመለከት ነው።

የግብጽ በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ እንቅስቃሴ ቀዳሚ ዓላማ የኢትዮጵያን የጂኦፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መገደብ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ከሱዳን፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ ጋር ያደረገቻቸው ስምምነቶችም ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትገለል ከማድረግ ባሻገር፣ በቀጣናው ግብጽ ብቸኛ ተሰሚነት ያለው ሃይል ሆኖ መውጣትን ያለመ ነው፤ የኢትዮጵያን የቀጣናው ሀያልነት ለማስቆም የሚደረግ ጫናና የፖለቲካ ስልት ነው፤ አይሳካም እንጂ።

የግብጽ ባለስልጣናት አካሄድ “ዓይናችሁን ጨፍናችሁ እናሞኛችሁ” የሚል ስሁት የፖለቲካዊ አመለካከት መገለጫ ነው። አዲስ የቀጣናውን ሃይል ለመቀየርና በራስ ቁጥጥር ስር ለማድረግ የመሞከር ዝንባሌ ነጸብራቅ ነው። በ21ኛ ክፍለ ዘመን ወደ ጋርዮሽ ስርዓት የመመለስ ህልም፤ ዛሬም በቅኝ ግዛት አስተሳሳብ የመመራት የበታችነት ስሜት መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ሁለተኛው ነጥብ ግብጽ ለሱዳን፣ ለኤርትራና ለሶማሊያ ሕዝቦች ያላት ንቀታዊ ምልከታ ያሳያል፤ በሌሎች ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተደራድሮ የራስን ጥቅም ብቻ የማስጠበቅ የራስ ወዳድነት በሽታ ማሳያ ነው። ግብፅ የቀይ ባህርም ሆነ የዓባይ ተፋሰስ ጥያቄን ደጋግማ ስታነሳ ከፖለቲካዊ ፍላጎት ውጭ መሬት ጠብ የሚል የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የለውም። የሶማሊያ ኤርትራና ሱዳን ሕዝቦችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ማህበራዊ ለውጥ ማረጋገጥ የሚያስችል አይደለም።

አራቱ ሀገራት ያደረጉት ስምምነት በኢኮኖሚው መስክ መሬት ጠብ የሚል ጠቀሜታ አያመጣም። ምክንያቱ ደግሞ የግብጽ ኢኮኖሚ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ካለው የንግድ ልውውጥ ይልቅ የጂኦፖለቲካ አጋርነት በመፍጠር የቀጣናውን የኃይል ሚዛን ወደራሷ ለመጎተት መሻት ፍላጎት ነው። የግብጽ ጥረት የሀገራቱን የመልማት ፍላጎት መስዋዕት የማድረግ እኩይ ሴራ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ግብጽ ከሱዳን ወቅታዊ አለመረጋጋት እና ከኤርትራ ጂኦፖለቲካዊ አቋም ጋር ራሷን በማቀናጀቷ በእርሷ ጥላ ሥር እንዲቆዩ አድርጋ ዘመናዊ ቅኝ ገዥ ሆና ተከስታለች። የእነዚህ ሀገራት ህዝቦች ግብጽ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስትራቴጂያዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ በመሪዎቻቸው ተላልፈው የተሰጡ የመስዋዕት በጎች ሆነዋል።

የግብጽ አካሄድ ዜሮ-ድምር ጨዋታ (Zero-sum game) መርህን የተከተለ ነው። የሌሎችን አገሮች ፖለቲካዊና ስትራቴጂያዊ ድጋፍ ለማግኘት የምታሳየው ጥረት የኢኮኖሚ ውህደትን ማምጣት አይደለም። ይልቁንስ በዓባይ ተፋሰስ እና በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ ላይ ያላትን የበላይነት ከማስቀጠል የሚመነጭ ሴራ ነው። ይህ ደግሞ የቀጣናውን ህዝቦች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል።

ኢትዮጵያ ከግብጽ ራስ ወዳድና “ባልበላውም ጭሬ ልድፋው” ከሚለው አመለከካት ፍጹም የተለየ አቋም አላት፤ ለጎረቤቶቿ ልዕልና የቆመች መሆኗንም በተደጋጋሚ አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን በላባቸው፣ በደማቸውና በእውቀታቸው የገነቡት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከሚያመነጨው የኤሌትሪክ ሃይል ለጎረቤቶቿ በመስጠት በሃይል አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጋለች። ቃሏን በመጠበቅ የጎረቤት ሀገሮቸ ህዝቦች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትተጋለች። በጋራ ማደግን ሰንቃ ትሰራለች።

የኢትዮጵያ የትብብር ጥረቶች ወደ መሬት ወርደው የቀጣናው ሀገራት የሚያጋጥማቸውን የኑሮ ውድነት ማቃለል ያስችላሉ። የንግድ ትስስርን ያጠናክራሉ፤ ለልማትና ለሰላም መሰረት ይጥላሉ።

በአንፃሩ የግብጽ ጫናዎችና ጥምረቶች ከራሷ ፍላጎት ማሟላት ነው፤ ይሄውም የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና መከፋፈል፣ ለውጥረትና ለውጭ ጣልቃ ገብነት ማጋለጥ፣ ለጂኦ ፖለቲካ ፉክክር ማቃጠጠያ መሳሪያ መሆን ነው።

የግብጽን እኩይ አካሄድ የቀጣናው ሕዝቦች ተረድተው በቃ የሚሉበት ጊዜ አሁን ነው። ከብሔራዊ ጥቅማቸው ይልቅ ለግብጽ ያልተገታ ፍላጎት ያጎበደዱ መሪዎቻቸውን የሚጠይቁበት፣ “ለእኛና ለልጆቻችን ምን ጥቅም የሚሰጥ ስምምነት እያደረጋችሁ ነው” በማለት የሚያፋጥጡበት ወቅቱ ዛሬ ነው።  ለሌላ ሀገር “የበላይነት የመሆን” ቅዠት እውን መሆን የሚዳክሩ መሪዎቻቸውን መጠየቅ ግድ ይላቸዋል። እነርሱ እየተራቡ ሌላው ሊፈነጭ አይገባም። በፍጹም።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም