ምክር ቤቶቹ የተጣለባቸውን ሀገራዊ አደራ በብቃት በመወጣት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቶቹ የተጣለባቸውን ሀገራዊ አደራ በብቃት በመወጣት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ምክር ቤቶቹ የተጣለባቸውን ሀገራዊ አደራ በብቃት በመወጣት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ ፤ታላቅ ርዕይ
ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።
በዚህም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎቻቸውን በመሰየም ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል።
በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸው እንደገለጹት፤ የታላቁ ህዝብ ምክር ቤት የመንግስት ስልጣን መሰረቱ እና ምንጩ የሰፊው ህዝብ የይሁንታ ድምጽ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሕያው ምስክር ነው።
የህዝብ ምክር ቤት አባላት የሚያከናውኗቸው ተግባራት እና የሚደነግጓቸው ህጎች በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የስልጣን ፍኖት በህዝብ የይሁንታ ድምጽ እና ተቀባይነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመልክተው፤ ሕዝብ የጣለባችሁ ሀገራዊና ህዝባዊ ሀላፊነት በእጅጉ ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ስለዚህ የህዝቡ ይሁንታ ከአመኔታ ጋር ታላቅ አደራን መስጠቱን እንደሚያረጋግጥ አመልክተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ሀላፊነት በታላቅ አስተዋይነት፣ ጥበብ፣ ብልሃትና ታታሪነት እንደምትወጡት ያምናል ብለዋል።
ሁለንተናዊ ዝግጅታችሁ ይህንን አደራ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን ከፍ ወደአለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ጭምር ሊሆን ይገባል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው።
የምክር ቤት አባላቱ ቀዳሚ ትኩረት መልካም አስተዳደርን የሚያዘምን፣ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በይበልጥ ከፍ የሚያደርግ፣ ምርት እና ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ የኑሮ ውድነትን የሚገራ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ይበልጥ የሚያስፋፋ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በስፋት የሚዘረጋ፣ የህዝብን ሰላም እና ደህንነት የሚያጸና መሆን እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።