የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የጋራ ሀላፊነት ነው - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የጋራ ሀላፊነት ነው - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ብልፅግናን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የጋራ ሀላፊነት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ ፤ታላቅ ርዕይ
ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።
በዚህም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎቻቸውን በመሰየም ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰይመዋል።
በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት ንግግር፤ ሀገሪቱ በየዘመኑ ሲንከባለል የመጣው የአመፅ ፖለቲካ ተግባር የሚያከትምበት እና የልማትና የሰላም ድምፅ የሚሰማበት ጊዜ ላይ ደርሳለች፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላምና የተረጋግቶ የመኖርን ዋጋ በጥልቅ የሚያውቅ፣ የጦርነትን ክፋትና አጉዳይነት በጉልህ የሚረዳና የሚጠየፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉትና በታከቱ እሳቤዎች ሕዝብን ወደ አመፅ አዙሪት ለማስገባት የሚደረጉ ማናቸውም ሙከራዎች መደምደሚያቸው መቃረቡንም አስገንዝበዋል።
የሁከት ኃይሎች በየጊዜው የጋረጧቸውን ፈተናዎች መንግስት በትዕግስት፣ በስክነት፣ በብርታት እና በጥብቅ ኃይል ጭምር ማምከን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን የሚመጥናት ጎዳና ዕድገት፣ ብልጽግና እና አንድነት በመሆኑ መንግስትና ማህበረሰቡ የሴራንና የግጭት ነጋዴዎችን አምርረው እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
የታላቅ ሀገርና የነባር ስልጣኔ ባለቤት የሆነ ህዝብ መገለጫ ሀገርን ማጽናት፣ ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ሰላምን መጠበቅ በመሆኑ የተጀመሩት የምርት ጉዞዎች ያላንዳች ማወላወል እንደሚቀጥሉ በስራና በትጋት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያዊነት እሳቤ በየእያንዳንዱ ጋሬጣ የሚደናቀፍ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ታላቁን ሀገራዊ ርዕይ እና አቅም ከፍ አድርጎ በማየት ላይ ያተኮረ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።
በዚህ መንገድ የተጀመሩ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ዕይታዎች የታላቅነት ሀሳብ የወለዳቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ምንጊዜም ከእውነት እና ከታሪክ ትክክለኛ ጎን የሚሰለፍ አስተዋይ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግስት ይህንኑ እሴት ያከብራል፣ ይጠብቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያውያንን ሰላም መጠበቅ እንዲሁም ብልፅግናዋን ማረጋገጥ የመንግስት ተግባር ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የጋራ ሀላፊነት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ጥሪት ጠብቆ የማቆየት፣ የማስቀጠል እና የማሻሻል የጋራ ሀላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።