ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የታላቅነት መንገድ የሚያስፉ አስተማማኝ ተቋማት እየተገነቡ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የታላቅነት መንገድ የሚያስፉ አስተማማኝ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገልጸዋል።

ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ 

ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።

በዚህም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎቻቸውን በመሰየም ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰይመዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ መርሐ ግብር ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በመቋቋም ጠንካራ ተቋማትን እየገነባች ነው ብለዋል።

በስትራቴጂክ እይታ የሚመሩ ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ተግባራትም በሕዝብ አንድነት ላይ የተመሰረተ ታላቅ ሀገራዊ ስኬትና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን እያረጋገጠች መሆኑ ገልጸዋል።

መንግሥት የኢትዮጵያን የትልቅነት መንገድ የሚያስፉ ዘላቂና ሁለንተናዊ ተቋማትን በማደራጀት የላቁ አቅጣጫዎችንና ተግባራትን ቀይሶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን የታላቅነት መንገድ የሚያስፉ አስተማማኝ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደትም ማህበራዊ እሴቶችን በማስተሳሰርና በሃሳብ የበላይነት በማመን ሕብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያንና ጠንካራ ወንድማማችነትን ለማረጋገጥ መሰረት እንደጣለ አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም