ቀጥታ፡

ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች ለቀጣይ አፈጻጸም ጠንካራ መሠረት ፈጥረዋል - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች ለቀጣይ አፈጻጸም ጠንካራ መሠረት መፍጠራቸውን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ። 

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ህዝብ ፤ታላቅ ርዕይ

ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ 

ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።

በዚህም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎቻቸውን በመሰየም ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰይመዋል።

በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በግብርና፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በወጪ ንግድ፣ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በዲጂታል መሠረተ ልማት የተከናወኑ ተግባራት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል።

የግብርና ሥርዓቱን ለማሻሻል አዳዲስ ቴክኖሎጂና ግብዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል፣ የመስኖ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የማምረት አቅምን ማሳደግና የማዕድን ዘርፉን ማስፋፋት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ከፍ ካደረጉ ሥራዎች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

የወጪ ንግድና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች መበልጸግና የቱሪስቶች ቁጥር መጨመር፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት መስፋፋትና የአገልግሎት ዘርፉ ምርታማ መሆኑ በአጠቃላይ የሀገሪቷ የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ከፍ እንዲል ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።

መንግሥት ባወጣው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ በመመራትና የባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ እሳቤና ግብን በመከተል የመንግሥትን የገቢና የታክስ ሥርዓት በማጠናከር የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ መቻሉንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

መንግሥት አዋጭነት የሌላቸውን የንግድ ብድሮች በማስቀረት ሀብትና ጊዜ ያባክኑ የነበሩ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዳይስተጓጎል መደረጉን ጠቁመዋል።

የሀገሪት የኢኮኖሚ ዕድገት ለረጅም ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየውን ሥራን በጥራት የመከወንና ውጤታማ የማድረግ ፈተና በአዲስ ተነሳሽነት፣ ተከታታይነትና ኢላማን ስኬታማ ባደረገ መንገድ ማከናወን መቻሉ ለውጤቱ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ትልቅ የዕድገት አቅምና ጥሪት የሆነው ማኅበረሰብ አቀፍ ተሳትፎን የሚያበረታታ የሥራ አካሄድ መከተሉ የመፈጸም አቅምንና ልምድን ለማዳበር ማስቻሉን ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።

የሕዝቡ ተሳትፎ ማደጉም በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የሀገሪቷን የደን ሽፋን በጉልህ ለማሳደግ ያስቻለ ታላቅ አብነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ያስመዘገቡ የከተሞች የተጠናከረ የጽዳትና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም በርካታ የሀገር መሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና ተጓዦች የሚጠቅሷቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አብነት የሚነገርላቸው ስኬቶች መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

መንግሥት ያወጣቸውን ዕቅዶች ለመፈጸም መትጋቱና ማኅበረሰቡ በተለያዩ ተነሳሽነቶች ሀሳቡን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ሳይቆጥብ በማበርከቱ የተገኘው ውጤት የላቀ ሊሆን መቻሉን ፕሬዚዳንት ታዬ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም