ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገትና ግስጋሴ የሚያመላክቱ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ታላቅ የኢኮኖሚ ዕድገትና ግስጋሴ የሚያመላክቱ ስኬቶች መመዝገባቸውን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ አካሄደዋል።

ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።

በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያን የእድገት እርምጃ እና ግስጋሴ በሚቆጠሩ እና በሚለኩ አመልካቾች ማሳየት ተገቢ ይሆናል ብለዋል።

የ2018 ዓመታዊ የሰብል ምርት ከሰባት ዓመት በፊት በ2011 ከነበረው 335 ሚሊዮን ኩንታል ዓመታዊ የሰብል ምርት ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ኩንታል መድረሱ የዚህ ግስጋሴ ታላቅ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ አንድ ቢሊዮን የሰብል ምርት እድገት ማስመዝገብ ታላቅ እምርታ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ልዕል ነው ብለዋል።

የወጪ ንግድ ገቢ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 11 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም የኢትዮጵያ የእድገት እርምጃና ግስጋሴ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ እድገት 15 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉም ከሚጠቀሱ ስኬቶች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።

የብድር አቅርቦት ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር ማደጉ፣ የዋጋ ንረት ዝቅ እንዲል መደረጉን አስታውሰው፤ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ገቢ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ትሪሊየን ብር መድረሱ ከሚጠቀሱ ስኬቶች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም