የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ሁለገብ ጥረት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ሁለገብ ጥረት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ ፈተናን የሚቋቋም ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ሁለገብ ጥረት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ሰባተኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።
ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ማካሄዱ ይታወቃል።
በዚህም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎቻቸውን በመሰየም ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰይሟል።
በምክር ቤቶቹ የጋራ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ዕድገት ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በመቋቋም የተመዘገበ ታላቅ ቁምነገር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞም ፈተናዎችን የሚቋቋም ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ሁለገብ ጥረት ተጨማሪ ብልሃትና አቅም የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር ሁሉንም የጥንካሬ አቅሞች በማደራጀት ዕድገትና ብልጽግናን የሚያፋጥኑ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ልምምድ ለማዘመንና የሰከነ የፖለቲካ ግንኙነት እንዲኖር መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች አዲስ ባህልና ልምምድ መፍጠራቸውን አንስተዋል።
በሌላ መልኩም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ መቀረጹ የሀገርን ጥቅሞች ከማስከበር ባለፈ አያሌ ወዳጆችና አጋሮችን ለማበራከት እንዳስቻለ ጠቅሰዋል።
ይህም የደህንነትና የፀጥታ ዘርፎች በማዘመን፣ የትምህርትና የጤና፣ የከተማና የገጠር ልማቶች ከሕዝብ መሰረታዊ ጥቅሞች ጋር በማስተሳሰር ጉልህ ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ እመርታዎችም ሀገራዊ ከፍታና ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷን የሚያጠናክሩ የወል ሃሳቦችን የሚያጸኑ፣ ሉዓላዊነትን በጠንካራ ውቅርና አምድ ላይ የሚያቆሙ፣ ዕድገትና ብልጽግናን የሚያበስሩ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸው አብራርተዋል።