ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግባለች

የታላቋ ሀገር ፤ ታላቅ መንግሥት

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግባለች። ትናንት በይፋ የተመሰረተው የመደመር መንግሥትም ከ54 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በነፃና በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሰጡት ድምፅ የቆመ፣ የሕዝብን አደራና እምነት ሙሉ በሙሉ የተረከበ ታላቅ መንግሥት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ ባደረጉት ንግግር፡ "ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ፣ የዲሞክራሲ ባህልም የሚፈተነው በምርጫ ወቅት ነው፤ ያሳለፍነው ምርጫ እንደማንኛውም ህዝባዊ ምርጫ ተካሄደ ተብሎ ብቻ የሚገለጽ የሰርክ ኹነት አልነበረም" ብለዋል።

ዜጎች በምርጫው ፈቃዳቸውን ሊሰጡ የቻሉት በብዙ ውዥንብሮች መካከል አልፈው እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በየጫካው የሸመቁበት፣ በየሚዲያው እያዋከቡትና በአሉባልታ እያስፈራሩት እንኳን ሳይበገር ህዝቡ በብዙ ፈተናዎች መካከል አልፎ ህልውናውን ለማጽናት ፈቅዶ መምረጡን አስታውሰዋል። አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባህል መሰረቱ እየጠነከረ መምጣቱን በግልጽ የሚሳይ ከመሆኑም በላይ ወደፊት በደማቅ ብዕር የሚጻፍ ታሪክ ነው።

ዜጎች የመረጡት መንግሥት የመመሥረቱ ጉዳይ የምርጫ ሂደት ማጠቃለያ ብቻ ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ውሳኔ ሰጪነት ማረጋገጫ ነው።

ዜጎች የመረጡት መንግሥት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያደርጋቸው ማንኛቸውም ውሳኔዎች የሕዝቡን ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረጉ ናቸው። የዜጎች የምርጫ ተሳትፎ የመንግሥት ህጋዊነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገርን በጋራ የመገንባትና የሉዓላዊነት ባለቤት የመሆን ትልቅ ማሳያ ነው።

የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የሕዝብን ዘላቂ ተስፋና ሀገራዊ እድገት እውን ያደረጉ በርካታ ታላላቅ የመሠረተ ልማት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሴክተር ስኬቶችን ማበሰር የቻለ ነው። በተለይም የሕዝብን የዘመናት ጥያቄዎችን የመለሱ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና በውጤታማነት በማጠናቀቅ አቅሙን ለዓለም አሳይቷል።

የገበታ ለሀገር፣ የገበታ ለትውልድ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለዜጎች ምቹ የኑሮ ሁኔታንና የሥራ ዕድልን ፈጥረዋል። በስንዴ ምርት የተመዘገበው ራስን የመቻልና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ስኬት፣ ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተደረገ ትልቅ እርምጃ ነው።

የኢትዮጵያውያን የጋራ አቅምና የፅናት ምልክት የሆነው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለፍጻሜ በመቃረብ ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይልና የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በመሆን ላይ ይገኛል።

በተለየ ሁኔታ ይህ መንግሥት የሕዝብንና የሀገርን የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በፅናት እየሠራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በባሕር በርና በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ያላትን ፍትሐዊና ተፈጥሯዊ ፍላጎት በግልጽ ብሔራዊ ጥቅም አድርጎ በማስቀመጥ፣ በበሰለና በጠንካራ ዲፕሎማሲ ሀገራዊ መብቷን ለማስከበር የሚያደርገው ጥረት የሉዓላዊነታችንና የከፍታችን ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን በማስከበር፣ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በቀጣይነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ ውይይት በማድረግ ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን አከናውናለች።

በሕዝብ ድጋፍና በተመዘገቡት ታላላቅ የልማት ስኬቶች ታግዞ፣ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ አንድነትን እያጠናከረ ያለው ይህ መንግሥት፣ የታላቋን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በማስከበርና የወደፊት ብሩህ ተስፋዋን ይገነባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም