ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፅናት ጉዞ በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ጥሩነህ አንደበት

የተከበሩ አፈ ጉባኤ፣

ከብራትና ክቡራን የምክር ቤት አባላት፣ የተከበራችሁ ተጋባዥ እንግዶች፤

ዛሬ በተከበረው ምክር ቤት ፊት፣ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 73 ንኡስ አንቀጽ 2 መሰረት፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ እምነት አግኝቶ አብላጫ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያሸነፈው የብልፅግና ፓርቲን ወክዬ፣ አንድን ታላቅ የዘመናችን ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በዕጩነት ሳቀርብ ኩራትም፣ ክብርም፣ ዕድለኛነትም ይሰማኛል።

ፓርቲያችን ብልፅግና በዚህ የኢትዮጵያ ስልጣኔ መደላድል የሚፈጠርበት ወቅት፣ እኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያቀርብ የኢትዮጵያን ታላቅነት በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም ምን ያህል ቆራጥ አቋም እንዳለው ያሳያል።

ለኢትዮጵያ የተፈጠሩ፣ ለአገልግሎት የተጠሩ፣ መሰልቸት ያልፈጠረባቸው፣ ድካም የማያውቃቸው፣ አዲስ ነገር የማያልቅባቸው፣ ብዕር የማይነጥፍባቸው፣ ርህራሄ ገንዘባቸው፣ ፅናት መለያ ባህሪያቸው ነው።

ገና በልጅነታቸው ሀገር መውደድና ህዝብን ማክበር ከወላጆቻቸው የተማሩ፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ህዝቦችና ሃይማኖቶች ውስጥ ያደጉ፤ የሁሉም እንዲሆኑና ሁሉንም እንዲያገለግሉ አድርጎ ታሪክ የቀረፃቸው ናቸው።

በትንሿ የበሻሻ መንደር ሆነው ኢትዮጵያን አሻግረው ይመለከቱ ነበር። አንዴ ስታሳዝናቸው፣ አንዴ ስታስደስታቸው፣ አንዴ ሲቆረቆሩላት፣ አንዴ መልካም ሲመኙላት አንድ ቀን ለዚች ታላቅ ሀገር ደርሰው የታሪኳን ያህል ከፍ እንድትል፣ የፀጋዋን ያህል እንድትበለፅግ ይመኙ ነበር።

ለዚህ ነበር ሀገራቸውን በመስዋዕትነት ለማገልገል ወደ ትጥቅ ትግል ገና በ14 ዓመታቸው የገቡት። እርሳቸው እንደሆኑ ለኢትዮጵያ አይበጅም ብለው ያመኑበትን ነገር እስከመጨረሻው የመፋለም ባህሪ አላቸው።

የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ ወደ መደበኛው ወታደርነት ገቡ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በግንባር ተሰልፈው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከበሩ። የባድመ ግንባር የቀበሮ አሸዋ ውስጥ ሆነው ግን ያነቡ ነበር፣ ያስቡ ነበር፣ ያቅዱ ነበር፣ የለውጥ ሀሳቦችን ያወጡና ያወርዱ ነበር።

እስከ ሌፍተናንት ኮሎኔል የደረሰው የወታደርነት ጉዟቸው ኢትዮጵያን አሳምረው ያወቁበትና አውቀውም ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ያሰቡበት ምዕራፍ ነበር።

ዋጋ እየከፈሉ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ ሀገራቸውን አዩዋት። ሲያዩአት ደግሞ ፍቅሯ ባሰባቸው፣ ድካሟ አሳሰባቸው፣ ድህነቷ አስቆጫቸው። ትልቋ ሀገር ታላቅ አለመሆኗ እረፍት ነሳቸው።

በተለይም ደግሞ በሩዋንዳ ከተፈፀመው የእርስ በእርስ እልቂት ለማስቆም የተባበሩት መንግስታት ተልዕኮ አባል ሆነው ወደ ሩዋንዳ ሲዘምቱ ኢትዮጵያን እያነፃፀሩ መመልከት ጀመሩ።

ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን ካልጠበቅን፣ የሁላችንንም መብት ሁላችንም ካላከበርን፣ አንድነታችንን ኃይል፣ ብዝሃነታችንን ጌጥ ካላደረግን፣ በመመካከርና በመነጋገር ችግሮቻችንን ካልፈታን የእኛስ ዕጣ ፈንታ ከሩዋንዳ በምን ይለያል ብለው አሰቡ።

ከዚያ በኋላ በነበራቸው ጉዟቸው ይህንን እሳቤያቸውን ሲተረጉሙት ኖሩ። በሰላም፣ በንግግርና በአብሮነት ችግሮችን ፈትቶ አብሮ መኖር እንደሚቻል በትንሿ ከተማ በሻሻ በፈፀሙት አስደናቂ የሰላም ማስፈን ተግባር አረጋገጡ። በከተማዋ በዕምነት ስም ተነስቶ የነበረውን ችግር በንግግር፣ በምክክርና በይቅርታ ፈቱት።

ለዚህም ነበር አንገት ከሚቆርጠው ሰይፍ ይልቅ የሚያስታርቀው ሰይፍ፣ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር ይሻላል ብለው አምረው የተነሱት።

ከማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከሊድስታር ማኔጅመንትና የሥራ አመራር ኮሌጅ በለውጥ አመራር ኤምቢኤ (MBA)፣ ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ኤምኤ (MA)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደህንነት ጥናት ፒኤችዲ (PhD) አግኝተዋል።

ከብዙ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶች በተጨማሪ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸልመዋል።

ኢትዮጵያን የመለወጡም ምዕራፍ በቀድሞው የኦህዴድ አባልነትና አመራርነት፣ በኢንሳ መስራችነት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት በኩል ሞከሩት።

ሰዎችን ማፍራትና ሰዎችን መለወጥ፣ ከሙስናና ከአድሎ ነፃ የሆነ አመራርና አገልግሎት መስጠት፣ ከሁሉም ሰራተኞች ጋር እንደ ወንድም ሆኖ መስራት፣ የትኛውንም ኃላፊነት ሳይንቁ ለታላቋ ኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከል ማድረግ የዘወትር ህይወታቸው ነበረ።

ከስምንት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ለውጥ ትፈልግ ነበር። ድህነትና ኋላቀርነት ህዝቧን አስመረረው። መከፋፈልና መለያየት ህዝቡን አስጨነቀው። እድገቷ እየታነቀ፣ ብሶቷ እየታመቀ ሄደ። ፍታዊነት ጠፍቶ የአንዱ ወገን የበላይነት በርቶት ሀገር ተሰቃየች።

ፕሮጀክቶቿ ቆመው፣ መብቶቿ ታፍነው፣ እስር ቤቶቿ ሞልተው፣ የፖለቲካ ልዩነቶቿ ተካርረው ፈተና ውስጥ ወደቀች።

ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የለውጥ ሐዋርያም ፈለገች። ጦር የማይመዝ፣ አብዮት የማያስነሳ፣ ይውደምና ይቅደም የማይል፣ በአንደኛው መቃብር ላይ ሌላውን የማይገነባ፣ ህዝብን የሚያስተሳስር፣ አጋርና አካል አንድ የሚያደርግ፣ የሁሉንም ህዝቦች መብት በፍትሃዊነት የሚያስከብር፣ ከትናንት ይልቅ ነገ ላይ የሚያተኩር አዲስ መሪ ፈለገች።

በዚህ ጊዜ ከኦህዴድ አመራር ውስጥ፣ ከኢህአዴግ ልሒቃን መካከል፣ ከኦሮሞ ዕቅፍ፣ ከኢትዮጵያ ማህፀን አብይ የሚባል ሰው ተገኘ።

በጥበብና በብልሃት፣ በሰላማዊ ትግል ህዝብን በዓላማ በማሰለፍ፣ የህዝቦችን ህብረ ብሄራዊ ትስስር በማጠናከር፣ የአንድን ወገን የበላይነት በመታገል የታለመው ለውጥ እውን እንዲሆን አደረጉት።

ለውጥ በድርጅት ሳቢነት፣ በህዝብ ትግልና ገፊነት እውን ሆነ።

ኢትዮጵያ በተደጋገሚ ደም አፋሳሽና ሀገር አፍራሽ አብዮቶች አካሂዳለች። አሁን ግን በሪፎርም ሰንኮፏን ብቻ አስወገደች። ነባር አቅሞቿን እያፈረሰች መገንባት ተወች። ትናንት እንዳለ ማስወገድም ሆነ እንዳለ መቀበል አይጠቅመኝም አለች። በትናንት መሰረት ላይ ስብራቱን ጠግና፣ አረሙን ነቅላ ሌላ የነገ መንገድ ጀመረች።

የዛሬ ስምንት ዓመት በዚህ ፓርላማ ፊት የፈጣሪ ስም በክብር ተጠራ። ኢትዮጵያ በፍቅርና በክብር ተጠራች። ተቃዋሚዎች ተፎካካሪ ተባሉ። በጦርነት ውስጥ ለነበሩ ሁሉ የሰላም ጥሪ ተላለፈ። እናቶች ተከበሩ፣ ተመሰገኑ። ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የብልፅግና ጉዞ እንድታመራ ተበሰረ። በኢህአዴግ ስም የተፈፀመው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ተጠየቀ። ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር ታወጀ። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ አዲስ ነፋስ ነፈሰ።

እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እኚህ ሰው በሥራ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ልምምድ ፈጠሩ። ተፎካካሪዎችና ገዢው ፓርቲ አንድ መንግስት ሆነው እንዲሰሩ አደረጉ። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ተዘዋውረው ህዝብን ለሰላም፣ ለልማት ጋበዙ። አያሌ የፖለቲካ እስረኞች በምህረት እንዲለቀቁ አደረጉ። ሚዲያዎች በነፃነት ተከፈቱ። ከሀገር ውጪ ተሰደው የነበሩ ፖለቲከኞች ወደ ሀገር ገብተው በመንግስት ኃላፊነት እስከመመደብ ደረሱ።

ተለያይተው የነበሩትን የኦርቶዶክስ ሲኖዶስ አባቶችና የእስልምና ጉዳዮች አባቶች አስታረቁ። የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የወንጌላውያን ካውንስል በህግ እውቅና እንዲኖራቸው አደረጉ።

የፀጥታ አካላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እንዲሆኑና የህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ጠባቂዎች እንዲሆኑ አደረጉ።

የምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ሆኑ። ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ የማይመጥኑ አሳሪና ቀፍዳጅ ህግጋት ተሻሽለው የዳኝነትና የፍርድ ቤት ነፃነትና ገለልተኛነት ተከበረ። በየወረዳው እየዞሩ ከህዝብ ጋር ተመካከሩ። በደቡብ ኢትዮጵያ የነበረውን የክልልነት ጥያቄ እንዲፈታ አደረጉ።

የኢትዮጵያን አብዮት ከፖለቲካ አብዮት ወደ ስንዴና ሩዝ አብዮት ቀየሩት።

በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ የኢትዮጵያን ቅርሶች የሚጠብቅና አዳዲስ መድረሻዎችን የሚገነባ ኢኒሼቲቭን ፈጥረው ለፍፃሜ አበቁ።

ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያ፣ ለሌማት ትሩፋት፣ የገጠር ከተማ ኮሪደር፣ የበጋ ስንዴ፣ ንግድን በቀላሉ ማከናወን፣ ማዕድ ማካፈል፣ የክረምት በጎ ፈቃድ፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ኢኒሼቲቮችን ፈጥረውና መርተው ኢትዮጵያን ቀየሩ።

እየፃፉ፣ እያሳተሙ፣ እያሰለጠኑ ለኢትዮጵያ ብቁ አመራር ለመፍጠር ደከሙ። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን አመንጭተው በየክልሉ አዳረሱ። በአረንጓዴ አሻራ 56 ቢሊዮን ዛፎችን አስተከሉ።

አራት የመደመር መጻሕፍትን አሳትመው በተገኘው ገቢ በሁሉም ክልሎች ትምህርት ቤቶችን አስገነቡ።

ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት አቁማ በራሷ እንድታመርት አደረጉ። የፍራፍሬ ምርትን አሳድገው በውጭ ገበያ አበቁት። የማዕድን ምርታችን ከኋላቀርነት ወጥቶ የ100 ዓመታቱን የ5 ዓመት እንዲያስገኝ አደረጉ። ዲጂታል ኢትዮጵያን መርተው ገንዘብ በየሞባይላችን እንዲሆን አስቻሉ። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርተው የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ስብራት አቃኑ።

እልህ አስጨራሹን ትግል በድል ተወጥተው የህዳሴ ግድብን አጠናቀቁ። ኢትዮጵያ ጠንካራና የማይበገር ዘመናዊ መከላከያ እንዲኖራት አደረጉ።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ከሞት ተነስተው የኢኮኖሚው መሪ እንዲሆኑ አበቁ።

ጥንት ሀሳቡን ያነሱ፣ ውሾች ተብለው የተወገዙትን ሀገራዊ ምክክር አስጀምረው ለውጤት እንዲበቃ አደረጉ። አጋርና አካል የተባለው መለያየት ፈርሶ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ እንዲገነባ አደረጉ።

ከኮሮና ወረርሽኝ፣ ከተደጋገሚ ጦርነት፣ ከአንበጣ መንጋና ከድርቅ ፈተናዎች ኢትዮጵያን ታድገው ነጥረው እንደ አልማዝ ወጡ።

ገና በልጅነታቸው በኢትዮጵያ ላይ በክፉ የሚነሳ፣ እሳቸውም በደግ አያዩትም። በብዙ ነገር ይታገሳሉ፣ በብዙ ነገር ይሸከማሉ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከመጣባቸዉ ግን ማንንም አይሸከሙም። ለዚህ ነው ኢትዮጵያን እናጠፋለን ብለው ጠላቶች ቢነሱ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቢሯቸውን ትተው ክረቫታቸውን በፋቲክ ቀይረው ግንባር የዘመቱት።

እኚህ ሰው ኢትዮጵያን የባህር በር እንድታገኝ እየታገሉ ያሉ ናቸው። ኢትዮጵያ ታላቁን የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ እንድትገነባ እየመሩ ናቸው። ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል እየወጡ፣ እየወረዱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በዲጂታል ማንነት እንድትተሳሰር እያሰቻሉ ነው።

ኢትዮጵያ ትናንትን፣ ዛሬን፣ ነገን ያሰተሳሰረ ስልጣኔ እንድትገነባ መንገድ እየቀየሱ ናቸው። አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እርሻ ወደ ዘመናዊ ግብርና እንዲሸጋገር እያደረጉ ናቸው። አርብቶ አደሩ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲሸጋገር አዲስ የገጠር ስልት እያወጡ ናቸው።

ከተሜው ምቹ የክትመት ስርዓት እንዲኖረው ሌት ተቀን እየተጉ ናቸው። ለአብነትም አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ አበባ እናደርጋታለን ያሉትን ቃል በተግባር ያሳዩ እንቁ መሪ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያደርግ እያስቻሉ ነው። ተፎካካሪና ገዢ ፓርቲ በጋራ ሀገር የሚመሩበትንና በብሄራዊ ጥቅም ላይ በጋራ የሚሰሩበትን የፖለቲካ ምህዳር እያስለመዱ ነው። ትልቋን ኢትዮጵያ ታላቅ ለማድረግ ወገባቸውን አስረውና ጊዜያቸውን ሁሉ ሰውተው እየሰሩ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አካሄድ ከጠላትና ወዳጅ ዋልታ አውጥተው ገቢር ነበብ እያደረጉት ነው።

ለዚህ ነው ዛሬ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ምክር ቤት ፊት እንዲሰየሙ የተከበሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድን በዕጩነት የማቀርበው።

ለውጥን አስበው፣ ለውጥን መርተው፣ ለውጥን ኖረው አሳይተዋል። የተወለዱት በኦሮሚያ ክልል፣ ጂማ ዞን፣ በበሻሻ ከተማ ሲሆን አሁን እድሜያቸው 50 ደርሷል። በዚህ ውስጥ ሦስት አራተኛውን ለሀገር አገልግሎት አውለዋል። ባለትዳር የአራት ልጆች አባትና የሚሊዮኖች ወዳጅ ናቸው።

የተከበረው ምክር ቤት እኚህ ባለብዙ ፀጋ የኢትዮጵያ ልጅ በለውጥ ጉዞ ተፈትነው እንደ ወርቅ ነጥረው የወጡትን፣ በታሪክ ውስጥ ማለፍ ብቻ ሳይሆን የታሪክን ማርሽ የቀየሩትን፣ ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ፈልጋ ያገኘቻቸውን ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ አሊን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ፓርቲያችን ብልፅግና በዕጩነት ሲያቀርብ በታላቅ ክብርና ኩራት እንዲሁም ዕድል ነው።

አመሰግናለሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም