ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ስልጣኔ የመገንባት ርዕይ በተግባር የሚገለጥ የትውልድ ቃል ኪዳን ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን ስልጣኔ እንገነባለን ስንል ተራ ፉከራ ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ የትውልድ ቃል ኪዳንና  በተጨባጭ የሚሳካ ግዙፍ ህልም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ባደረጉት ንግግር፤ ሰዎች ራዕይ አንግበው ዓለም ክብ ናት ሲሉ፣ ምድርን ለማሰስ ሲነሱ፣ ጨረቃን ለመርገጥ ሲጓዙ፣ አውሮፕላን ሲሰሩ፣ ስልክ ለመፍጠር ሲሞክሩ ሁሉም ህልመኞች ተብለው እንደነበር ገልጸዋል።

ነገር ግን ዛሬ የእነሱ ህልም እውን ሆኖ ትውልድ እየኖረው፤ የኛም ህልም ልጆቻችን በተግባር የሚኖሩት የተስፋ አድማስ ሆኗል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የምግብ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ ከልመና ለመውጣት፣ የበጋ ስንዴ ልማት ሲጀመር፣ ለዘመናት ያንቀላፉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ሲነሱ፣ ከተሞችን ለማዘመን በኮሪደር ማልማት ሲጀምሩ "ህልመኞች" ተብለው እንደነበርም አስታውሰዋል።

ጅምሩ እውን ሆኖ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ አስቀርቷል፣ ከተሞችን አዘምኗል፣ ሕዳሴ ግድብን ከሞት ቀስቅሷል፡ መገጭና ርብ ግድቦችን አስነስቷል፣ ጣና በለስን ወደ ምርት አስገብቷል ብለዋል።

አዲሱን የኢትዮጵያ ስልጣኔ እንገነባለን ስንል ተራ ፉከራ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተግባር የሚገለጥ የትውልድ ቃል ኪዳንና  በተጨባጭ የሚሳካ ግዙፍ ህልም መሆኑን ገልጸዋል።

የከተሞች ለውጥ ከአህጉር ተሻግሮ የብዙዎች መነጋገርያ መሆኑን ገልጸው፤ የቀጣዩ ዕቅድ በመደመር እሳቤ ዕውን እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው እያሉ ከበሮ ሲደልቁ የነበሩ ጠላቶች ህልማቸው ቅዠት ሲሆን ዛሬ ደግሞ ጭንቀታቸው ኢትዮጵያ በቀይ ባህር እንዳትነግስ መገደብ ሆኗል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በመጣንባቸው መንገዶች በልበ ሙሉነት ከተጋን ህልማችንን መኖርና ማውረስ እንደምንችል በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን አሳይተዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ እንደ ታላቅ፣ ኃያልና የስልጣኔ ቀንዲል መሆኗን በማንሳት፤  የቀጣናውን ህዝቦች  የምታነሳ ወሳኝ ሀገር እንደምትሆን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም