ቀጥታ፡

መደመር የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል አረጋግጠናል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-መደመር የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል አረጋግጠናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ ለተደጋጋሚ ጊዜያት የኢትዮጵያን ለውጦች የሚገፋቸው ቁጭት እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓትን የመገንባት ሙከራዎች የቁጭት ችግር ባይኖርባቸውም የእፎይታና የስክነት ችግር ይስተዋልባቸው እንደነበር አስረድተዋል።

የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ለኢትዮጵያ የሚሆነውን አዋጭ መንገድ መርጦ፣ ፈትኖና አረጋግጦ ኢትዮጵያዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም እንደነበርም ገልጸዋል።

በዚህም የየወቅቱ መሪዎች ከሚያዋጣው መንገድ ይልቅ አቋራጩን ሲመርጡ በመኖራቸው የኢትዮጵያን ችግር ለሌሎች ተቀድቶ በተሰፋ የውጭ ሀገር እሳቤ ለመፍታት ሲሞክሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ምንጩን የሚረሳ ወንዝ ይደርቃል እንዲሉ መሰረቱን፣ ባህሉን፣ ልማዱን፣ ሀገራዊ እሳቤውን በማሽቀንጠር የሚጀምር የሥልጣኔ ጉዞም ሩቅ ሊጓዝ አይችልም ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።

ለዚህም ባለፉት ስምንት ዓመታት በሥልጣኔ ጉዟችን ለሚገጥሙን ፈተናዎችና እንቅፋቶች መሻገሪያ የሚሆን የጥበብ ወረት እንዳለን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊ እሳቤ እንደነበረን አረጋግጠናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ይህም የመደመር እሳቤ ነው ብለዋል።

የአውሮፓ ሥልጣኔ የተገነባው በአውሮፓዊ ባህል፣ የኤስያ ሥልጣኔም በኤስያዊ ባህል በተስማማው በኮንፊሺየስ እሳቤ ላይ ተመስርቶ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ባለፉት ዓመታት የሌሎችን ተሞክሮ ከራሳችን ጋር ስናስማማ ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ መደመር የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል አረጋግጠናል ብለዋል።

የምንኮራባቸው ሥልጣኔዎቻችን ሁሉ በመደመር እሳቤ የተቀኙ እንደነበሩ በመገንዘብ በለውጡ ጊዜ የተሞከሩ ተግባራት አስደናቂ ውጤት ማምጣት እንደቻሉም አብራርተዋል።

ከፋፋይና ጠባብ እሳቤዎችን በሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲተኩ የተደረገው የሀገር በቀል እሳቤ ሙከራ ፍሬ እያፈራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም