ኢትዮጵያ ፈጣን የጂኦፖለቲካ ለውጦችን በመገንዘብ ከቀድሞ ልምዶቿ በመማር በቂ ዝግጅት ማድረግ አለባት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፈጣን የጂኦፖለቲካ ለውጦችን በመገንዘብ ከቀድሞ ልምዶቿ በመማር በቂ ዝግጅት ማድረግ አለባት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ በአካባቢዋና በዓለም የሚታዩ ፈጣን የጂኦፖለቲካ ለውጦችን በመገንዘብ ከቀድሞ ልምዶቿ በመማር በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተከናውኗል።
አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምስራቅ አፍሪካና የቀይ ባህር ቀጣና ከፍተኛ የጂኦፖለቲካ ለውጥ እያስተናገደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ከፈተና ባሻገር እድልም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ መገናኛ፣ የባብ ኤል መንደብ የባህር መስመር እና የመካከለኛው ምስራቅ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ቀጣናውን የዓለም አቀፍ የሀያላን ፉክክር ማዕከል እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ሳያሳድር ሊያልፍ እንደማይችል ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሀያላን ፉክክር የቀጣናውን የፖለቲካ ሁኔታ መቀየሩንም ተናግረዋል፡፡
አቅም በነበረን ወቅት የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን ወስነናል፤ በተዳከምን ጊዜ ግን ሌሎች በእኛ ላይ ወስነውብናል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በአሁኑ የዓለም ሥርዓት ለውጥ ወቅት ፈጥና መንቃት፣ የራሷን አቅም መገንባትና የሀገራዊ ጉዳዮቿን በራሷ አቅም ለመወሰን መዘጋጀት እንደሚገባት አስገንዝበዋል።
በማዕበል የምትናጥ ዓለም ውስጥ እስከምን ለመጓዝ ተዘጋጅተናል? ሲሉ ያነሱት ጥያቄ፣ ከሚመጡ ፈተናዎች ጋር በጥንካሬ ለመጋፈጥ የሀገሪቱ ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑን ያመላክታል።