በፍጥነት እና በፈጠራ መንገድ ሪፎርም እያደረግን፣ የሚመጣውን ዓለም ለመቃኘት እየተዘጋጀን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በፍጥነት እና በፈጠራ መንገድ ሪፎርም እያደረግን፣ የሚመጣውን ዓለም ለመቃኘት እየተዘጋጀን ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-ያለፉትን ስብራቶች መርምረን፣ በፍጥነት እና በፈጠራ መንገድ ሪፎርም እያደረግን፣ የሚመጣውን ዓለም ለመቃኘት እየተዘጋጀን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
በዚህም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ በመፈጸም ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ ካለፉት የታሪክ ተሞክሮዎች በመማር የዓለምን ፈጣን ለውጥ ቀድሞ መረዳትና ለሚመጣው ዘመን በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዓለም በተከታታይ የኢንዱስትሪ አብዮቶችን በማካሄድ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ አቅሟን ስታሳድግ፣ ለእነዚህ ለውጦች ራሳቸውን ያዘጋጁ ሀገራት የአብዮቶቹ ተዋናዮች መሆን መቻላቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ከእነዚህ ለውጦች በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷን ጠቅሰው፣ በተለይ በጦርነትና በውስጣዊ ግጭት የተነሳ ከዓለም የለውጥ ጉዞ ጋር በተመጣጣኝ ሁኔታ መጓዝ እንዳልቻለች አስታውሰዋል።
ቀድሞ አለመዘጋጀት እንደሀገር የሚያስከፍለውን ዋጋ ለማሳየትም የጣሊያን ዳግም ወረራን በምሳሌነት አንስተዋል።
በዓድዋ ጦርነት የተሸነፈው የጣሊያን ሀይል አራት አስርት ዓመታት ያህል የሚቆይ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በአንጻሩ ከዓድዋ ድል በኋላ በበቂ ሁኔታ ሳትዘጋጅ መቆየቷ በማይጨው ጦርነት ከተለወጠው የጦር ቴክኖሎጂ ጋር እንድትጋጠም መገደዷን ገልጸዋል።
በወቅቱ ወራሪው ሀይል 450 ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ይዞ ሲመጣ፣ ኢትዮጵያ ከ12 በማይበልጡ ወታደራዊ ያልሆኑ አነስተኛ አውሮፕላኖች ለመጋፈጥ መገደዷንም ነው ያነሱት።
በመሆኑም ካለፉት የታሪክ ተሞክሮዎች በመማር የዓለምን ፈጣን ለውጥ ቀድሞ መረዳትና ለሚመጣው ዘመን በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ገልጸዋል።
አንድ እንቅፋት አንዴ መመታት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ደጋግሞ መመታት ግን የጤና እንዳልሆነ በመጥቀስም ያለፈውን በመረዳት የተሻለ ዝግጅት ማድረግ የሀገሪቱን ቀጣይ ጉዞ ለማሳካት ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ የት ላይ እንዳለች በመገምገም የሚመጡ ለውጦችን ቀድማ በመጠበቅና በመዘጋጀት በዓለም የለውጥ ጉዞ ውስጥ ተዋናይ ሆና መቀጠል እንዳለባትም ነው የተናገሩት።