ኢትዮጵያውያን ሀገር አጽንተው ለትውልድ ማስተላለፍ የቻሉት በመደመር እሳቤ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ሀገር አጽንተው ለትውልድ ማስተላለፍ የቻሉት በመደመር እሳቤ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በመቋቋም ሀገር አጽንተው ለትውልድ ማስተላለፍ የቻሉት በመደመር እሳቤ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ የ2010 ዓ.ም ለውጥን ያመጣው በአዲስ ትውልድ ውስጥ ያለው ዓለምን አሸንፎ የመጓዝ ፍላጎት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ለውጦች የሚገፋቸው ሀገር ወደኋላ ስትቀርና ዓለም ወደፊት ሲራመድ የሚፈጠር ቁጭት እንደነበር ጠቁመው፤ ከባዱ ነገር ይህንን ቁጭት በተገቢው ስርዓት የማስተናገድ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።
ቁጭት መነሻ እንጂ መድረሻም ሆነ ማድረሻ እንደማይሆን ገልጸው፤ ማድረሻው ሥርዓት ሲሆን መዳረሻው ደግሞ ስልጣኔ መሆኑን ተናግረዋል።
ቁጭት ስርዓትን እንዲወልድ ሰክኖ ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ መመርመር፣ መሞከር፣ የተሻለውን መምረጥና ማሻሻል አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሥርዓት በአንድ ጀምበር ተገንብቶ እንደማያልቅና ይልቁንም በሂደት የሚፈጠር፣ ትዕግስት እና ትጋትን እኩል የሚጠይቅ፣ ጥበብ እና ስክነትንም አጣምሮ የያዘ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓትን የመገንባት ሙከራዎች የቁጭት ችግር እንዳልነበረባቸው ገልፀው፤ በአንጻሩ ግን በአንድ በኩል የእፎይታ እና የስክነት ችግር እንደሚስተዋልባቸው ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለአዲስ ሀሳብ ዝግ የመሆን ጠባይ በሰፊው እንደሚታይም በንግግራቸው አንስተዋል።
ነባራዊውን ዓለም ተገንዝቦ ለኢትዮጵያ የሚሆነውን አዋጭ መንገድ መርጦ፣ ያንን መንገድ ፈትኖ እና አረጋግጦ ኢትዮጵያዊ ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ዝግጁነት እንደሚያንስም ጨምረው አስታውቀዋል።
በዚህም ምክንያት የየወቅቱ መሪዎች ከሚያወጣው መንገድ ይልቅ አቋራጩን ሲመርጡ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የሀገራችንን ችግር በውጭ ሀገር እሳቤ ለመፍታት ሲጣደፉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያን ከዚህ አዙሪት ለማውጣት ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን ጠቁመው፤ በስልጣኔ ጉዟችን ውስጥ ለሚገጥሙን እንቅፋቶች መሻገሪያ የሚሆን የጥበብ ወረት መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
ፈተናዎች ያልበገሩት፣ ችግሮች ያልበጠሱት፣ ርዕዮተ ዓለሞች ያልቀየሩት፣ የውጭ ወራሪዎች ያልሰበሩት ኢትዮጵያዊነት ሊገኝ የቻለው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንገድ ስለሚጓዙ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ይህም ብዝሃነትን ከአንድነት፣ የእምነት ልዩነትን ከእሴት ትስስር፣ አካባቢነትን ከሀገር፣ የግል ፍላጎትን ከቡድን፣ ትናንትን ከዛሬ፣ አቅምን ከአቋም ደምረው ስለሚጓዙ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
ያለንን የስልጣኔ ወረት ይዘን፣ የስረ መንግስትነት እሴታችንን አዘምነን፣ በሀገር በቀል እሳቤ ላይ የታነጸ ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ እንዳንገነባ የሚከለክለን ማንም የለም ብለዋል።
በትውልድ ቅብብሎሽ የደለበውን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ወረት ፈልፍለን፣ ከባህር ማዶ የምናገኛቸውን ጠቃሚ ጥበቦች ከኢትዮጵያዊ እሳቤ ጋር በማጣጣም ስልጣኔ መገንባት እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የሌሎችን ተሞክሮ መርምሮ ከራሳችን ጋር እንዲስማሙ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ መደመር የኢትዮጵያ ስልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።
የምንኮራባቸው ስልጣኔዎቻችን ሁሉ በመደመር እሳቤ የተቃኙ እንደነበሩ መታወቅ መቻሉን ጠቁመው፤ በለውጡ ጊዜ የተሞከሩ ተግባራት አስደናቂ ውጤት ማምጣታቸውንና ከፋፋይ እና ጠባብ እሳቤዎች በህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲተኩ ተደርገው ፍሬ ማፍራት መቻላቸውን አስታውቀዋል።