ቀጥታ፡

አለመግባባቶችን በጠብመንጃ ለመፍታት የሚደረግ አካሄድ ተገቢ አይደለም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት እየተቻለ በጠብመንጃ ለመፍታት የሚደረግ አካሄድ ተገቢ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ፈተናዎች ወደኋላ የሚጎትቷት ሀገር አይደለችም ብለዋል።

ለአብነትም በምግብ እራሷን ለመቻል ያደረገችው ጥረት ከራሷ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል የግብርና እመርታዊ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

ዛሬ ላይም የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ያለን አማራጭ በዓላማ በመጽናት ሀገርን የሚለውጡ ስራዎችን መስራት ሀገራዊ ግዴታችን እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የምክር ቤት አባላትም የኢትዮጵያን ስልጣኔ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ጠንካራ ርዕይ በመሰነቅ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ስልጣኔ፣ አስደናቂ ታሪኮችና እሴቶች ያላት ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ድንቅ ሀብቶችን በማልማት የተጀመሩ ልማቶችን ማስቀጠል ላይ ክፍተት እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያን ዕድገት በማፋጠን የድኅነት ተጋላጭነትን ማስወገድ እንደሚገባ በመጠቆም፤ አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት እየተቻለ በጠብመንጃ ለመፍታት የሚደረግ አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራትን ሊመግብ የሚችል የእርሻ መሬትና ልዩ ልዩ የሰብል አይነቶች ያላት ሀገር ሆና ሳለ በምግብ ራሷን ለመቻል ፈተና ሆኖባት እንደቆየም አስታውሰዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያዊያን በጋራና በትብብር ያሉብንን ችግሮች ቀርፈን የሰለጠነች ሀገርን መፍጠር ይኖርብናል ብለዋል።

ድህነትን ማሸነፍ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የትምህርትና ጤና ተደራሽነት፣ ለኢንቨስተሮች ብድር ማመቻቸት፣ ቀልጣፋ ትራንስፖርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተደራሽነትም የቀጣይ ግቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዘላቂ ችግር የሚፈታው ኢትዮጵያ ስልጣኔ ስትገነባ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገርን ስልጣኔ ለማረጋገጥ ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ዓላማ በጋራ መስራትና መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የሰለጠነች ኢትዮጵያን በመገንባት ሀገሪቱን የምታሳድግ ብቻ ሳይሆን ዓለምን የምትቀይር ኢትዮጵያን መፍጠር ለነገ የማንለው የቤት ስራችን ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም