አዲሱ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጾ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ መዘጋጀት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጾ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ መዘጋጀት አለበት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-አዲሱ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጾ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ መዘጋጀት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰባተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
በዚህም ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛ ጊዜ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ሁሉም ዜጎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶች አባቶችና እናቶች ለሀገር እድገትና አንድነት በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በጫካ የሚገኙ የታጠቁ አካላት ይህንን ታሪካዊ እድል በመጠቀም ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቅሬታ ያላቸው ወገኖችም የይቅርታን መንፈስ ተላብሰው በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ ጥቅም ላይ በጋራ የመቆም እና በአማራጭ ሀሳቦች የመፎካከር ባህልን ማሳደግ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
አዲሱ ትውልድ በእውቀት፣ በክህሎት እና በስነ-ምግባር ታንጾ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመረከብ መዘጋጀት እንዳለበት ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፤ የዛሬ ወጣቶች በሩቅ አሳቢነት ነጋቸውን እንዲቀርጹ አሳስበዋል።
የትናንት ወጣቶች ካለፈው ስህተታቸው በመማር ከአብዮታዊ የትግል ስልትና ከባንዳነት ልምምድ በመራቅ የተጣሉትን ለማስታረቅና የሸሹትን ለመመለስ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የሀገር አባቶችና እናቶችም ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅነትና ስልጣኔ በመጸለይ ታሪካቸውን ማውረስና ትውልዱን መገንባት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
"ትናንት አልፏል፤ ነገም ገና አልደረሰም፤ ዛሬ ግን ምቹ ሆኖ ቀርቧል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬን በትጋት በመስራት ትናንትን ማስተካከል እና የፈለግነውን ዓይነት ብሩህ መንገድ መቅረጽ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኖረው ቆይታ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመጠየቅና ከመደገፍ ባሻገር የሚሰሩ ስራዎች ሁሉ የህዝቡን ህይወት ምን ያህል እንደለወጡና የመደመር ስልጣኔን ምን ያህል እንዳሳኩ በቅርበት እንዲከታተልና እንዲመራም አደራ ብለዋል።