ቀጥታ፡

ሀገራችን የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች መሻገር የምንችለው በወንድማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እኩል ስንራመድ ብቻ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ)፦ ሀገራችን የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች መሻገር የምንችለው በወንድማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እኩል ስንራመድ ብቻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በዚህም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ምርጫ አካሂደን፣ በህጋዊ ምርጫ እምነት ጥለው፣ በድምጻቸው መንግስት ለማጽናት በተግባር ለታመኑ ዜጎቻችን ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ፣ የዲሞክራሲ ባህልም የሚፈተነው በምርጫ ወቅት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያሳለፍነው ምርጫ እንደማንኛውም ህዝባዊ ምርጫ ተካሄደ ተብሎ ብቻ የሚገለጽ የሰርክ ኹነት አልነበረም ብለዋል።

ዜጎች በምርጫው ፈቃዱን ሊሰጥ የቻለው በብዙ ውዥንብሮች መካከል አልፎ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።

በየጫካው የሸመቁበት፣ በየሚዲያው እያዋከቡት፣ በአሉባልታ እያስፈራሩት፣ በብዙ ፈተናዎች መካከል አልፎ ህልውናውን ለማጽናት ህዝቡ ፈቅዶ መርጧል ብለዋል።

አጠቃላይ ሂደቱ የዴሞክራሲ ባህል መሰረቱ እየጠነከረ መምጣቱን በግልጽ አሳይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ወደፊት ታሪክ በደማቅ ብዕር እንደሚጽፈው፣ ትውልድም ደጋግሞ እንደሚዘክረው ጥርጥር የለኝም በማለት ገልጸዋል።

ማንኛውም ምርጫ አሸናፊ እና ተሸናፊ ፓርቲ ሊኖረው ይችላል፤ ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ዜጋ እንደማይኖራት በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

ሀገራችን የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች መሻገር የምንችለው በወንድማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን እኪል ስንራመድ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ፤ ዛሬ ዘመኑ ተቀይሯል ነገሮች እንደ ድሮ አይደሉም ብለዋል።

ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎች በፍጥነት እንደሚለዋወጡ ጠቅሰው፤ ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወዲህ የዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መልኮች በፈጣን ለውጥ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።

ዓለም በጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቿ ምክንያት መልክ እና ጠባይዋ መቀያየሯን ጠቁመው፤ አይገመቴነት የዘመኑ ዋነኛ መገለጫ እየሆነ ነው፤ ቋሚ አሰላለፍ ማየት ብርቅ ሆኗል ብለዋል።

የባለብዙ ዓለም ዋልታ ሊወለድ በሚታገልበት በዚህ ወቅት ጎራ መርጦ ማንም እንደማይቆምና የትኛውም ፖለቲካዊ እሳቤ በዓለም ላይ እንደሚነግስ ከግምት በዘለለ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።

ታሪክ ወደ የትኛው አዲስ ምዕራፍ እንደሚያደርሰን በግልጽ በማይታወቅበት መንታ መንገድ ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዲስ ነገር ዕዳም፣ ምንዳም አለው፤ ዕዳ እና ምንዳው ግን ለሁሉም እኩል አይደለም ነው ያሉት።

መጪውን ዘመን ቀድመው አስበው፣ የሚመጣውን አዲስ ነገር ከወዲሁ ገምተው፣ በጥንቃቄ ለሚጠብቁ ብርቱዎች ምንዳው ብዙ መሆኑን ጠቁመው፤ በአንጻሩ ዘግተው እና ተዘናግተው ለሚቆዩ ደካሞች ዕዳው እልፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የሀገራችን አርሶ አደርም «መጪው ክረምት የሚጠቅመው ላረሰው ገበሬ ነው» እንደሚል ገልጸው፤ ከሁለቱ አማራጮች ለሀገራችን የሚበጀውን መንገድ መርጦ መከተል የዚህ ትውልድ ታላቁ አደራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም