ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ትሰራለች 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በዚህም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በቀጣዮቹ ዓመታት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዋን በሚያሳድግ መልኩ ይቃኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን መሰረት አድርጋ በጋር እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።

ጎረቤት ሀገራት በተፈጥሮ የተገናኙ ወዳጆች መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  ከሁሉም ጋር በሰላም፣ በጋራ ጥቅም እና በትብብር የመስራት መርሃችን እንገፋበታለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባህር በር እውን ሊሆን አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የዓለም እና የአካባቢያችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የወደፊቱን የዓለም አካሄድ ያገናዘበ የመከላከያ ሃይል እንዲኖረን እንሰራለን ብለዋል፡፡  

ዘመናዊ፣ ፈጣሪ፣ ሁሌም ዝግጁ፣ ብቁና ንቁ፣ በየአውዶቹ የመሰማራት አቅምና ቁመና ያለው መከላከያ ይሆናል ብለዋል፡፡

ችግሮች ሳይፈጠሩ አስቀድሞ ማወቅና መግታት፣ ከመጡም መከላከል፣ ከባሰም እንደ አባቶቹ እንደ ልማዱ ማሸነፍ የሚችል ሃይል ሆኖ ይገነባል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የሃይማኖት፣ የሲቪክና የባህል ተቋማት ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች፣  ህብረ-ብሄራዊ አንድነቷ የጸና፣ ምርታማነትን ባህል ለማድረግ የምትተጋ፣ መሪና ፈር ቀዳጅ የሆነች አይበገሬ ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ዕድል ከፊታችን አለ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም