ለሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ለሆነው የወል ትርክት ግንባታ ተገቢ ትኩረት ይሰጠዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ለሆነው የወል ትርክት ግንባታ ተገቢ ትኩረት ይሰጠዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-ለሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ለሆነው የወል ትርክት ግንባታ ተገቢ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሄዷል።
አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሹመቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ የተጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የታለመለት ግብ እንዲመታ ይደረጋል ብለዋል።
ለዚህም የመደመር መንግሥት ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ያለበት የበጀት አካሄድን በመከተል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ለሕብረ ብሔራዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ የሆነው ለወል ትርክት ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
ምርታማነትን በሁሉም መስክ ለማላቅ ይሰራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የሰላም ሁኔታችንን የበለጠ ለማጽናት የውይይትና የይቅርታን መንገድ እንከተላለን ብለዋል።
የተጠናከረ የጸጥታና የደህንነት ዝግጅትና ክትትል እንዲሁም ስምሪት በአስተማማኝ መሰረት የማነጽና የመገንባት ሥራ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።
የመገናኛ ብዙኅን ምህዳርንም ሕግን፣ ሀገራዊ እሴቶችንና ፍላጎቶችን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚሰራበት አንስተዋል።