የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የሚገነባውን ትውልድ ለመፍጠር አበክረን እንሰራለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የሚገነባውን ትውልድ ለመፍጠር አበክረን እንሰራለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-የትምህርት ጥራትን የበለጠ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የሚገነባውን ትውልድ ለመፍጠር አበክረን እንሰራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
በዚህም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የትምህርት ጥራትን የበለጠ በማስቀጠል የኢትዮጵያን ሥልጣኔ የሚገነባውን ትውልድ ለመፍጠር አበክረን እንሰራለን ብለዋል።
ለዚህም የመደመር መንግሥት ህብረተሰቡ በሞራል፣ በእሴት፣ በክህሎት እንዲሁም በሀገራዊ ስሜት የሚታነጽበት መንገድ እንደሚከተል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለድርቅ፣ ለጦርነት፣ ለኢኮኖሚ ቀውሶች፣ ለጂኦፖለቲካዊና ሌሎች ፈተናዎችና ተግዳሮቶች የማትበገር እንድትሆን የሚያስችል የሁለንተናዊ የዝግጅትነት አቅም እንደሚገነባም አስረድተዋል።
የሲቪል አገልግሎት አሰጣጥ በሂደት ሳይሆን በውጤትና በተጽዕኖ የማዘመን ተግባርም ተጠንክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ባህልና ስነ-ጥበብ ለሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ለህዝቦች ትስስርና ለኢትዮጵያ መለያና ግንባታ ተገቢውን ሚና እንደሚጫወት በሚያስችል መንገድ ድጋፍ እንደሚደረግ አንስተዋል።
በተለያየ ዓለማት የሚኖሩ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በሀገሩ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ኑሮ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥረት እንደሚደረግም አብራርተዋል።