ቀጥታ፡

ከተሞቻችን ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለቱሪዝም የተስማሙና ተምሳሌት በመሆን የሚጠቀሱ እየሆኑ ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-ከተሞቻችን ለመኖሪያ፣ ለንግድና ለቱሪዝም የተስማሙና ተምሳሌት ተደርገው የሚጠቀሱ እየሆኑ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመሥረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

በዚህም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ዓመታት ተረስተው የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች ተጠግነውና ተሻሽለው ለጎብኚዎች ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡  

ከዚህ በፊት የማይታወቁ የሀገሪቱ ሀብቶች ታድሰውና ለነገው ዘመን ተዘጋጅተው ተጨማሪ ሀብት ማመንጨት ጀምረዋል ነው ያሉት። 

ዛሬ ከተማና ገጠሩ እኩል እየተቀየረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሞቻችን የዘመናዊ ከተማ መልክ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል። 

በዚህም ለመኖሪያ የተመቹ፣ ለንግድና ኮንፈረንስ የተስማሙ፣ ተምሳሌት ተደርገው የሚጠቀሱ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው ዛሬ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ውብ አበባ ተብላ ብትጠራ እውነት እንጂ ባዶ ምኞት ተደርጎ አይወሰድም ነው ያሉት። 

የአዲስ አበባ ለውጥ የዓለም ጎብኚዎችን ኑ ወደ እኔ እያለ ሲጠራ፤ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምርት ባህላችንን ሲያድሰው፤ የማዕድን ልማታችን የዘመናት የወጪ ንግዳችንን በአጭር ጊዜ መብለጥ ሲችል አይተናል ሲሉም ተናገርዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው በአረንጓዴ አሻራ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ስንተክል የተራቆቱ ሜዳዎቻችን አረንጓዴ ለበሱ፤ ተጠርጎ የሚሸሸው አፈር ባለበት ተገደበ ሲሉም አክለዋል።

የበጋ መስኖ ልማት የኢትዮጵያን የስንዴና የሩዝ ታሪክ መቀየሩን ጠቁመው በሌማት ትሩፋት የወተት፣ የዶሮና የዕንቁላል ምርቶች እንደጨመረና ይህም በምግብ ራስን የመቻል ግብ ሩቅ እንዳልሆነ ጠቁሞናል ብለዋል። 

መሶብ የአንድ ማዕከል የኢትዮጵያን የአገልግሎት አሰጣጥ መልክ ማስተካከሉን ጠቁመው ፋይዳ አዲሱን ዲጂታል ማንነት ማጠናከሩን፣ የወንዝ ዳር ልማት የኢትዮጵያን የውሃ እሳቤ መቀየሩን እንዲሁም የገበታ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ነባር መልኮች በአዲስ መልክ ሲገልጡ በአይናችን አይተናል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም