ቀጥታ፡

በሀገር ግንባታ ላይ እየጎለበተ የመጣው የወጣቶች ተሳትፎ

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ  

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተከናወኑ ሀገራዊ ሂደቶች ወጣቶች በፖለቲካና በምርጫ፣ በሀገራዊ ምክክር፣ በቴክኖሎጂ እና በሥራ ፈጠራ፣ በስፖርት፣ በባህልና ኪነ-ጥበብ፣ በሰላም ግንባታና በበጎ ፈቃደኝነት የሚያሳዩት ተሳትፎ እየጎላ መጥቷል።

ይህ ሁኔታ ወጣቶች በሀገራዊ ልማት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ሀሳብ የሚያመነጩ፣ በውሳኔዎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሳተፉና በዛው ልክ ተጠቃሚነታቸውንም እያረጋገጡ የሚሄዱ የዛሬ ተዋናዮች የነገ ደግሞ ተረካቢዎች መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።

ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የታየው ሰፊ የወጣቶች ተሳትፎ ነው። በምርጫው ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች ተሳትፈዋል። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ሰፊውን ድርሻ ወጣቶች ሊይዙት እንደሚችልም ይታመናል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከሚጎለብትባቸው ሂደቶች መካከል ምርጫ አንዱ ነው። በዚህ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ላይ ወጣቶች በተመራጭነት፣ በመራጭነት፣ በምርጫ አስተባባሪነትና አስፈጻሚነት፣ በፖለቲካዊ ውይይቶችና በተለያዩ የሕዝብ ተሳትፎ መድረኮች ላይ በንቃት መሳተፋቸው ወጣቶች በሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ አሳይተዋል። ይህም ወጣቶች የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን ከሩቅ የሚመለከቱ ሳይሆኑ በሂደቱ ውስጥ በቀጥታ የሚሳተፉ ዜጎች መሆናቸውን ያሳያል።

ሀገራዊ ምክክር፤ የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ የታየበት ሀገራዊ ሁነት

የወጣቶች ተሳትፎ በምርጫ ብቻ ሳይወሰን በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በግልጽ ተንጸባርቋል። በሀገራዊ ምክክሩ ከተካተቱ የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶች ዋነኞቹ ነበር። ባገኙት ዕድልም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተመለከቱ በርካታ አጀንዳዎችን በማቅረብ ተሳትፏቸውን አጠናቀዋል። 

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ በጋራ የሚያገናኙ ጉዳዮችን በውይይት መለየት፣ በልዩነቶች ላይ መነጋገርና በሀገር ደረጃ መግባባት የሚፈጥሩ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ነው። በዚህ ሂደት ወጣቶች መሳተፋቸው በዲሞክራሲያዊ ውይይትና በሰላማዊ የሀሳብ ልውውጥ ውስጥ ያላቸውን ሚና ያሳያል። በመሆኑም ሀገራዊ ምክክር ወጣቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበትና ሀሳባቸውን የሚያንጸባርቁበት መድረክ መፈጠሩን ያሳያል።

ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ፈጠራ 

የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ተሳተፎ እና ተጠቃሚነት በግልጽ ካሳየባቸው ዘርፎች መካከል የቴክኖሎጂ ዘርፍ አንዱ እና ዋነኛው ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ የወጣቶች ተጠቃሚነት በቴክኖሎጂ ፈጠራም የታጀበ ነው። የዲጂታል ዘመኑ ለወጣቶች አዳዲስ የተሳትፎ መድረኮችን ፈጥሯል። በኮዲንግ፣ በሶፍትዌር ልማት፣ በዲጂታል አገልግሎት፣ በፊንቴክ፣ በኢ-ኮሜርስና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ወጣቶች አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅና መፍትሔዎችን በማቅረብም ጭምር።

መንግሥት  የወጣቶችን በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳደግ ካለው መሻት የተነሳ የ5 ሚሊየን ኮደሮች ፕሮግራም ነድፎ በመተግበር ውጤት አስመዝግቧል። ወጣቶችን በኮዲንግና በዲጂታል ክህሎት ለማብቃት የተሄደበት ርቀት እና የተመዘገበው ውጤት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ ተሳትፎ ወጣቶች ቴክኖሎጂን ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ቴክኖሎጂን ወደ መፍጠር እንዲሸጋገሩ፣ ችግሮችን የሚፈቱና ሥራ የሚፈጥሩ ምቹ ዕድል ፈጥሯል።

ቴክኖሎጂን ለስራ ዕድል ፈጠራ

ወጣቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ። በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መጥቷል። ወጣቶች ቴክኖሎጂን ለግብርና፣ ለአግሮ-ቢዝነስ፣ ለማምረቻው ዘርፍ፣ በኢ-ኮሜርስ እና ለአገልግሎት ዘርፎች ዕድገት በማዋል በኩል የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱም ናቸው። ይህም የወጣቶች ሚና ከሥራ ፈላጊነት  ወደ ሥራ ፈጣሪነትና ወደ ንቁ ኢኮኖሚያዊ ተዋናይነት እየተሸጋገረ መምጣቱን ያመለክታል።

ስፖርት፤ የወጣቶች ተሳትፎ ሌላው መድረክ

የመደመር መንግሥት በአእምሮም በአካልም የጎለበተ ትውልድ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖረውን አበርክቶ በውል በመረዳቱ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሆኑ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል። እየሰራም ይገኛል። ስፖርት ወጣቶች ሀገራዊ ተሳትፏቸውን የሚያጎለብቱበት እና ሀገራቸውን በዓለም የውድድር መድረኮች ላይ የሚወክሉበትና የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው። የስፖርት ተሳትፎ ከውድድርና ውጤት ባለፈ የቡድን ሥራ፣ የመከባበር፣ የደንብ ማክበርና የሰላማዊ ውድድር እሴቶችን የሚያጎለብት በመሆኑ ለዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታም አስተዋጽኦ አለው።

ባህልና ኪነ-ጥበብ፤ የወጣቶች የሀሳብ መግለጫ

ወጣቶች በባህልና ኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እያሰፉ ነው። በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በቲያትር፣ በስዕልና በሌሎች የፈጠራ ዘርፎች የሚሳተፉ ወጣቶች የራሳቸውን ሀሳብና እይታ ለማህበረሰቡ እያቀረቡ የሌሎችንም እየወሰዱ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የራሳቸውን ጠጠር እንዲያኖሩ ዕድል የሚፈጥሩ አውዶች ናቸው። ኪነ-ጥበብ ሀሳብን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ፣ ልዩነቶችን ለማቀራረብና የጋራ እሴቶችን ለማጠናከር ከሚያገለግሉ መድረኮች አንዱ በመሆኑ፣ የወጣቶች በዚህ ዘርፍ መሳተፍ ለሀገራዊ ማንነትና ለማህበራዊ ትስስር ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

ሰላም ግንባታና በጎ ፈቃደኝነት፤ ለማህበረሰብ ተሳትፎ

የወጣቶች ሀገራዊ ተሳትፎ በሰላም ግንባታና በበጎ ፈቃደኝነትም ጭምር ይገለጻል። በተለያዩ የሰላም ማስፈን፣ የማህበረሰብ ውይይት፣ የአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ድጋፍ ሥራዎች ወጣቶች በበጎ ፈቃድ የሚሳተፉባቸው ዘርፎች ናቸው። ይህ የወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ለሀገር ጉዳይ መቆም እንደሚችሉ ያሳያል።

በጎ ፈቃደኝነት በተለይ የዜግነት ተሳትፎን በተግባር የሚያሳይ መስክ ነው። ወጣቶች ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለማህበረሰቡ በማበርከት የጋራ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያሳያሉ። ይህም የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎን የሚያጠናክር ነው።

ይህ ሁለንተናዊ የወጣቶች ተሳትፎ ለሀገራዊ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውጤታማነት አይነተኛ ሚና አለው። የመደመር መንግስት በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገር ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ ተጠቃሚነታቸውንም እንዲያረጋግጡ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

ወጣቶች ይህን ትልቅ ዕድል በመጠቀም ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ከመጠቀም ባለፈ ለሀገር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ዕድል በሚገባ ከተጠቀሙበት የኢትዮጵያ ወጣቶች የነገ ተስፋ ብቻ ሳይሆኑ በዛሬው የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ አሻራቸውን ማኖር ያስችላቸዋል።

የወጣቶች ተሳትፎ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ብቻ ሳይሆን በሀገራዊ ልማት፣ በሰላም፣ በማህበራዊ ትስስርና በፈጠራ ዘርፎች እየሰፋ የመጣ ግልጽ እውነታ ነው። ይህን ተሳትፎ በተጠናከረ መንገድ ለማስቀጠል ዛሬ የሚመሰረተው የመደመር መንግስት ግልጽ አቅጣጫ ይከተላል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም