ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል - የማድረግ አቅም ዳርቻ

በብዙ መውጣትና መውረድ፣ ውስጥ አልፏል። በውድ መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስከብሯል። በሁለት አሳዛኝና አስገራሚ አጋጣሚዎች የመፍረስ አደጋ ተደቅኖበት ነበር፤ አሳዛኙ በጣሊያን ወረራ ወቅት ወድሞ ከጥቅም ውጭ መሆኑ ነው። ሁለተኛውና አስገራሚው ነገር ደግሞ በ1983 ዓ.ም መንበረ ስልጣኑን በሀይል የተቆጣጠረው ጸረ ኢትዮጵያው ሕወሓት የባህር ኃይሉን ሙሉ በሙሉ በመበታተን የአየር ኃይሉን በማዳከም ለሀገሩ ያለውን ጥላቻ የገለጠበት የታሪክ አጋጣሚ ነው። 

የመፍረስ አደጋዎችን በማለፍ የማንሰራራት ዘመንን ዋጅቷል። የቀጣናው የሰላም ዘብ፣ የደህንነት ዋስትና መሆኑን በጀግንነት እያሳየ ድፍን 90 ዓመታትን ተሻግሯል፤ አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር ኃይል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ “ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር በጠቅላላ ነው የተበተነው፤ ኢትዮጵያ መልሳ ማግኘት የማትችላቸው ንብረቶች ወደ ጎረቤት ሀገር ተበትነዋል።” ብለዋል። ሕገወጡ ሕወሓት ምድረ በዳ ያደረገው አየር ሀይል ዛሬ ፈተናዎችን በጽናት ተሻግሮ ድል የማብሰር ምልክት ሆኗል።

የጠንካራና አይበገሬ ተቋማት፣ የሉዓላዊነት ዋስትና የድል አድራጊነት አውራ ሆኗል። “ሰማዩ የእኛ ነው” በሚል መሪ ሀሳቡ እንደ ስሙ እያደረ ነው። የቀጣናው አስተማማኝ የሰላም ዘብ ነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል። የአውሮፕላን አብራሪዎችና ቴክኒሻኖችን ማሰልጠኛ ማዕከል፣ ለሌሎች የሚተርፍ የጥገና አቅም ገንብቷል፤ መለዋወጫዎችን ያመርታል። ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የታጠቁ የሰማይ ላይ ንጉሶችን አፍርቷል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሰው ልጅ የማድረግ አቅምና ብቃት የታየበት፣ የዳበረ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለበት የቴክኖሎጂም፣ የምርምርም፣ የውጊያም፣ የሰላምም ተቋም ሆኗል። ነገን መዋጀት፣ ኢትዮጵያን ማፅናትና ማስቀጠል የግብሩ መገለጫ መሆኑን አንስተዋል። የኢትዮጵያ ልጆች የጀመሩት ለውጥ በትናንሽ ሙከራዎች ሸብረክ የማይል በጽኑ መሰረተ ላይ የመገንባቱ ማረጋገጫ ማህተም ጭምር።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1928 ዓ.ም ሲቋቋም የመጀመሪየው አዛዣ ሻለቃ ሚሽካ ባቢቼፍ ነበሩ። የመጀመሪያዋ የጦር አውሮፕላን ደግሞ "ንስረ ተፈሪ" /Nessre Tafari/ የተሰኘችው ባለሁለት ክንፍ የፈረንሳይ ስሪት Potez 25-ናት። ኢትዮጵያ ከብዙ የዓለም ሀገራት በፊት ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ባንክና መሰል ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎት ስትጀምር የኢፌዴሪ አየር ኃይል አንዱ ነበር።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት አርማ፣ የሉዓላዊነትና የደህንነት ማረጋገጫ ማህተም መሆኑን በሰማይ ላይ ነግሦ በተግባር አረጋግጧል፤ እያረጋገጠም ይገኛል። ዛሬ የኢትዮጵያ የአየር ክልል በአስተማማኝነት በመጠበቅ የሰማይ ንግሥናውን ተቆናጧል። የኢትዮጵያ የታላቅነት ማንፀሪያ ሆኖም ያገለግላል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ “90 ዓመታትን በተሻገረው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ታሪክ ውስጥ የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል በደምና በአጥንታቸው ሀገር ያጸኑ ጀግኖቻችንን አፍርቷል” ብለዋል። የለውጡ መንግሥት አየር ኃይሉን ከመፍረስ ታድጎ በውጊያ መሰረተ ልማት፣ በሰው ኃይል ግንባታና ትጥቅ በማሟላት ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም ገንብቷል። 

የኢፌዴሪ አየር ኃይልን በሁሉም ረገድ በማዘመንና ሁለንተናዊ ብቃቱን በማሳደግ የመከላከያ ሠራዊቱ ጠንካራ ክንድ፣ የሉዓላዊነት ዘብ፣ የኢትዮጵያውያን ኩራት ማድረግ ተችሏል። አየር ኃይል ከ1969 – 1970 ዓ.ም በተካሄደው የእናት አገር ጥሪ /የኦጋዴን ጦርነት/ የእብሪተኛውን የዚያድ ባሬ ወራሪ ጦር ግብዓተ መሬት በማፋጠን የፈጸመው ጀብዱ በዓለም ወታደራዊ ኢላማና ስኬት ታሪክ እጅግ አስደናቂ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። 

እንደነ ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ባሉ ወደር የለሽ የአየር ላይ ቀዛፊዎች በቁጥር የላቀና ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶችን የታጠቀው የሶማሊያ አየር ኃይል ላይ የአየር የበላይነት በመውሰድ መቅሰፍት አውርደውበታል። ይህ ኢትዮጵያውያን በኩራት የሚናገሩለት ገናና ታሪክ ነው።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደ ታሪኩ ማደር የሚያስችለው ቅኝት ውስጥ ገብቷል፤ በጠላቶች የተቃጣበትን የመፍረስ አደጋ በጣጥሶ ወጥቷል። የአባቶቹ ልጅ መሆኑን አሳይቷል። ዛሬ እጅግ በረቀቁና በቴክኖሎጂ በዳበሩ የጦር ጄቶችና ሰው አልባ አውሮፕላኖች አቅሙን ገንብቷል። በጠላት ላይ ኢላማውን የጠበቀ ከፍተኛ አደጋ መፍጠር የሚችሉ ምስጉን ባለሙያዎችን አፍርቷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መሰረት ጌታቸው እንደሚሉት፤ የአየር ኃይል የጥገና፣ የማምረትና የቴክኖሎጂ አቅም በአፍሪካውያን ጭምር የተመሰከረለት አስደናቂ ለውጥ ውጤት አምጥቷል። በአፍሪካ ካሉ ትልልቅ የአቬዬሽን ኢንዱስትሪዎች አንዱ ሆኗል፤ በዕውቀት በቴክኖሎጂና ራስን በመቻል አቅም ልቆ ተገኝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል “የኢትዮጵያን አንድነትና ነጻነት ሊገዳደሩ የሚፈልጉ ሀይሎች አቅሟን አይተው እንዲገቱ፤ ከሞከሩም እንዲቀጡ የማድረግ ሀገራዊ አቅም ገንብቷል። ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አያውቅም፤ እናም አትሞክሩት፤ ሰላምን ማጽናት እንፈልጋለን ደፍሮ የሚሞክር ካለ ግን ግብዓተ መሬቱን እናፋጥናለን።” በማለት ኢትዮጵያ ግዙፍ ተቋም መገንባቷን አብስረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የተደረገው ስር ነቀል ሪፎርም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጥገና፣ የሰው አልባ አውሮፕላን ምርት፣ የመለዋወጫና ሌሎች የማምረቻ ፋብሪካዎች አቅም በፍጥነት አድጓል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል የማድረግ አቅም ጨምሯል፤ የትብብር ስምምነት በመፈራረም በጋራ ለመስራት የሚፈልጉ ሀገሮችም ተበራክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መሰረት ጌታቸው፤ ኢትዮጵያን የሚመጥንና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብር አየር ኃይል መገንባት እንደሚቻል የተረዳነው፣ ዐይናችንን የገለጥነው፣ ወደ ተግባር የገባነው ከሪፎርሙ በኋላ ነው ይላሉ። ሪፎርሙ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅና እንዲያለማ፣ ሀብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም በማድረግ ብዙ ሀብት እንዲያፈራ የማይገለጹ አቅሞችን እንዲገነባ ማድረጉንም አንስተዋል።

“የማምረት አቅማችን ከአምናው ዘንድሮ ጨምሯል” የሚሉት ምክትል አዛዡ፤ በቀን ከ20 ያልበለጡ ምርቶችን ከማምረት አሁን 350 ተሸጋግሯል፤ አንዳንድ መለዋወጫዎችን በቀን እስከ 3 ሺህ 500 የማምረት አቅም ገንብቷል፤ በኢትዮጵያ አየር ኃይል እርካታ የሚባል ነገር የለም፤ አይፈቀድምም። በድል ላይ ድል መጎናጸፍ፤ የኢትዮጵያን ሀያልነት ማወጅ የግቡ መዳረሻ ነው።

ስሙ በተነሳ ቁጥር ከኢትዮጵያ ውድቀት ጋር የሚቆራኘው ሕገ ወጡ ሕወሓት፤ ኢትዮጵያ ባህር በር አልቦ፣ ዜጎቿን የመልክዓ ምድር እስረኛ አድርጓል። ብርጋዴር ጄኔራል መሰረት ጌታቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አድማስ ተሻጋሪ ነው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ አይወሰንም፤ ህንድ ውቅያኖስ ይደርሳል፤ መሰረታዊ፣ ታሪካዊና ህጋዊ የባህር በር ባለቤትነቷ ምላሽ ማግኘት አለበት።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚመጠን አቅም ለመገንባት ሌት ተቀን መትጋት ደግሞ የአየር ኃይል አድማስ ተሻጋሪ የዘወትር ግብር ነው። ኢትዮጵያን የመታደግ፣ ኢትዮጵያን የማኩራት፣ የተሰጠውን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ የመፈጸም ብቃት ተቋማዊ አርማው ሆኗል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር አስቀጥሏል። ኢትዮጵያ “ማህጸን ለምለም ናት” የሚለውን በገቢር እየኖረ ሰማዩን እያሰሰ አውሮፕላኑ እየተንደቀደቀ … የኢትዮጵያውያንን ልብ እያሞቀ … ቀጥሏል፤ ንሥርነቱን በተግባር እየገለጠ ወዳጆቹን እያስደመመ፣ ጠላቶቹን እያኮሰመነ ይቀጥላል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም