የታላቅ ሕዝብ ድምጽ - የጠንካራ ሀገረ መንግሥት መሠረት - ኢዜአ አማርኛ
የታላቅ ሕዝብ ድምጽ - የጠንካራ ሀገረ መንግሥት መሠረት
የታላቅ ሕዝብ ድምጽ - የጠንካራ ሀገረ መንግሥት መሠረት
ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ህዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ታላቅነት መታወቂያዋ፣ ግዙፍ ሕዝብ ጌጧ፣ አርቆ አሳቢ ርዕይ ደግሞ የጉዞዋ ኮከብ የሆነላት ኢትዮጵያ፣ በየዘመናቱ እንደ ተራራ የተደቀኑባትን መሰናክሎች ሁሉ ተሻግራ የልማትና የብልፅግና ጉዞዋን በጽናት ዘልቃለች። ዛሬም የጀመረቻቸውን ሀገራዊ የዕድገት ርምጃዎች አጠናክራ ለመቀጠል በታሪክ ማዕዘን ላይ ቆማለች። ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያሸጋግራትን መሪ የመምረጥ ባለቤትነትና ሥልጣን ለሕዝብ የተረጋገጠበት፣ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የዚህ ሀገራዊ ጉዞ ጉልህና ወሳኝ ምዕራፍ ሆኖ በታሪክ ማኅደር ሰፍሯል።
👉የታላቅ ሕዝብ ውሳኔ ትልቅነት
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በተከናወነው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው፣ ይበጀናል ላሉት ፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን በነጻነት ሰጥተዋል። በምርጫው 42 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። ይህ ተሳትፎም ምርጫውን በአገር ውስጥ የፖለቲካ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ ከተመዘገበባቸው ምርጫዎች ተርታ አሰልፎታል።
የምርጫው ስኬት በቁጥር ብዛት ብቻ አይለካም። ዜጎች የአየር ንብረት ተጽዕኖና የጊዜ ገደብ ሳይበግራቸው እስከ እኩለ ሌሊት ተሰልፈው ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ይህም ሕዝቡ ለሀገራዊ ዕጣ ፈንታው ያለውን ጥልቅ የኃላፊነት ስሜት፣ ትዕግሥትና ጽናት በተግባር የመሰከረበት፣ የታላቅነቱንም ምስክር ለዓለም ያሳየበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው።
የሕዝቡን ድምጽ ተከትሎም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 438 ወንበሮችን በማግኘት የአብዛኛውን ሕዝብ ይሁንታ በማግኘት ማሸነፉን ይፋ አድርጓል።
👉ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ተወካዮቹን የመምረጡ ዋና ዋና ጥቅሞች
ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ተወካዮቹን መምረጡ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እንደ ዓለት የጸና መሠረት ነው። የመንግሥት ጥንካሬ ምንጩ የሕዝብ ድጋፍና ይሁንታ ነው። የዜጎችን ይሁንታ ያገኘ መንግሥት ተቋማትን ለመገንባት፣ ሕግን ለማስከበርና ሀገራዊ አንድነትን ለማጽናት የሚያስፈልገውን ሞራላዊና ሕጋዊ መሠረት ይጨብጣል። ከፍተኛ የመራጮች ተሳትፎ የመንግሥትን ሕጋዊ ተቀባይነት ያጎላል፤ መንግሥትም "ሕዝብ የሰጠኝ አደራ ነው" ብሎ በሙሉ ልብ ፖሊሲዎቹን ይተገብራል፤ ዜጎችም ለወጡ ሕጎችና ውሳኔዎች ይበልጥ ይተባበራሉ።
ምርጫው የዴሞክራሲን ባህል በሕዝብ ልብ ውስጥ ይተክላል። ዜጎች ድምጻቸው ወሳኝ መሆኑን በዓይናቸው ሲያዩ፣ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን በልምድ ይገነዘባሉ። ይህ ልምድ ለመጪዎቹ ምርጫዎች ጠንካራ ፋና ሆኖ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ የሥልጣን ሽግግርን አገራዊ ባህል ያደርጋል። ከልዩ ልዩ ክልሎች፣ ማኅበረሰቦችና ሃይማኖቶች የተውጣጡ ዜጎች በአንድ ቀን፣ ለአንድ ዓላማ ወደ ምርጫ ጣቢያ መትመማቸውም "የጋራ ሀገር፣ የጋራ ዕጣ ፈንታ" የሚለውን ፅኑ ስሜት ያጎለብታል።
በመሰረቱ በካርዱ የመረጠ ዜጋ የመረጠውን መንግሥት የመከታተል፣ የመጠየቅና የመተቸት ሞራላዊ መብት ይጎናጸፋል። መንግሥትም ለመረጠው ሕዝብ የመመለስ ኃላፊነት ይሸከማል። ይህ የጋራ ተጠያቂነት የጤናማ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት የጀርባ አጥንት ነው። ግጭትና አለመግባባት በምርጫ ሳጥን ሲፈታም የሥልጣን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ መልስ ያገኛል፤ ይህም ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ዋስትና ነው።
በመጨረሻም ብዙ ሕዝብ የተሳተፈበት ምርጫ የሀገርን ዓለም አቀፍ ገጽታና ተዓማኒነት ያንጻል። ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ለኢንቨስተሮችና ለልማት ተባባሪዎች ያላትን ተዓማኒነት ከፍ ያደርጋል፤ የተረጋጋችና በሕዝብ ድጋፍ የምትመራ አገርም ለኢንቨስትመንትና ለትብብር ተመራጭ ናትና።
👉ከሕዝቡ ጠቀሜታ አኳያ
ምርጫ ለሕዝቡ የመብት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የጥቅሙም መሣሪያ ነው። ሕዝብ ሕልሙን፣ ፍላጎቱንና ምኞቱን እውን ያደርግልኛል ብሎ ያመነውን ፓርቲ መምረጡ ተገቢውን ምላሽ እንደሚያገኝ በማመን ነው። አሸናፊው ፓርቲም የሕዝብን ጥያቄዎች የመመለስ ቃል በትከሻው ላይ ይሸከማል። በዚህም ሕዝብ ፍላጎቱን የሚያስቀድም መንግሥት ያገኛል።
መንገድ፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የሥራ ዕድልና የኑሮ ውድነትን የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት ጥያቄዎች በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የመንግሥት ዕቅድ እምብርት እንዲሆኑ ድምጽ ተሰጥቷል። ይህም የልማትና የአገልግሎት ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙበትን በር ይከፍታል። ድምጹ ዋጋ እንዳለው ያየ ዜጋ ተስፋውና ተሳትፎው ይለመልማል። ዛሬ የሚጣሉ ጠንካራ ተቋማዊ መሠረቶችም ለልጆቻችንና ለመጪው ትውልድ የተረጋጋችና የበለጸገች አገር ቅርስ ሆነው ይተላለፋሉ።
👉የመደመር መንግሥት
ከ54 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሰጠው ድምጽ ውጤትን ከማብሰር ያለፈ፣ ከባድ አደራ የተሸከመ ነው። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተረጋገጠለት ብልፅግና ፓርቲ፣ ዛሬ መንግሥት የሚመሠርተው ይህንኑ የሕዝብ አደራ በመሸከም ነው። ዛሬ ለሕዝቡ ቃል የገባውን በተግባር የሚተረጉምበትን ፍኖተ ካርታ የሚያሳይበት ነው።
ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ እና የሀገርን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥም ተከታታይ ድሎችን እያስመዘገበ ያለ ፓርቲ ነው። ከድሎቹ ቀዳሚው የትውልድ ቃል ኪዳን የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም፣ ገንዘብና ጥረት የገነቡት ይህ ግድብ ተጠናቅቆ ተመርቋል። በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ሆኖም ለአገር ብርሃንን፣ ለሕዝብ ተስፋን፣ ለቀጣናውም የትብብር ዕድልን ይዞ ቆሟል። በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ተሰልፈው ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአገርን ገጽታ ቀይረዋል።
ስንዴን ከውጭ በማስገባት ትታወቅ የነበረች አገር፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ራሷን ወደ መቻል መንገድ ገብታለች። በኮሪደር ልማት የአዲስ አበባና የሌሎች ከተሞች ገጽታ ተለውጧል፤ ሕዝብም በንጹህ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ አካባቢ የመኖር መብቱን እያጣጣመ ነው። በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ለመገንባትና ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተጀመሩ ርምጃዎችም የአገሪቱን የነገ ከፍታ ያበስራሉ።
ሕዝብ አብላጫ ድምጹን የሰጠው ይህንን የስኬት ጉዞ አይቶ፣ ከዚህ የበለጠ ያደርሰናል ብሎ በማመን ነው። ስለዚህ የዛሬው ድምጽ ለፓርቲው ከዕውቅና ባለፈ፣ የጀመራቸውን ሥራዎች ወደ ከፍታ ለማድረስ የሚጓዝበት ስንቅ ነው። የተገኙት ድሎች የመጨረሻ መዳረሻ ሳይሆኑ ለቀጣይ ታላቅ ርምጃ የተቀመጡ መሠረቶች ናቸው። ፓርቲውም ይህንን የድል ጉዞ ሳይቋረጥ የማስቀጠል፣ ከፍ የማድረግና የማላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።
ዛሬ የሚመሰረተው የመደመር መንግሥት ሕዝብ በድምጹ በሰጠው ይሁንታ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የተቋም ግንባታና የሪፎርም ሥራዎች ሳይቆራረጡ እንዲቀጥሉ፣ ግልጽ የአምስት ዓመት የአመራር አቅጣጫም እንዲኖር ያስችላል።
ከሕዝብ፣ አደራ የተረከበው መንግሥት ሕዝቡ ያስቀመጠውን አደራ ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚለውጥበት ጊዜ ይመጣል። በኑሮ ማሻሻያ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር ይለወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሕዝብ እምነቱን አብላጫ ድምጽ በመስጠት ያረጋገጠው ፓርቲም ይህንን እምነት በውጤት የመመለስ ድርብ ኃላፊነት አለበት።
ጠንካራ ሀገር ከመገንባት አኳያም፣ ሕዝባዊ ይሁንታ ያለው መንግሥት፣ ጠንካራ ተቋማትና ንቁ ዜጋ ሲገናኙ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ይገነባል። ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ መርጧል፤ አሁን ደግሞ ምርጫው የዘራውን ተስፋ በሥራ የማጽናት ኃላፊነት ብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ነው። ያለፉት ድሎች ለቀጣዮቹ ስኬቶች መወጣጫ ደረጃ ሆነው፣ ሕዝብና መንግሥት በመተማመን ላይ የተመሠረተ የጋራ ጉዞ ሲያደርጉ፣ ኢትዮጵያ ታላቅ ሕዝቧን እና ታላቅ ርዕይዋን የሚመጥን ከፍታ ላይ ትደርሳለች።