ዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ባህል ግንባታን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ባህል ግንባታን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በታዳጊዎች ላይ በትኩረት በመስራት የሳይንስ ባህል ግንባታን የሚያጠናክሩ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ገለፁ።
ዩኒቨርሲቲው የዲጂታላይዜሽን ዘርፉን የሚመሩ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የታዳጊዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት የሚያሳድጉ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
ዩኒቨርሲቲው በክረምት ወቅት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን አንስተው፤ ባለው የስቴም ማዕከልም ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር የሚያዩበትና የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ተማሪዎች የሚጎበኙት የሳይንስ ሙዚየምም የሳይንስ ክህሎትን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የልህቀት ማዕከላት ፈጠራን የሚያበረታቱ በመሆናቸው በተማሪዎችና መምህራን የተሰሩና ወደ ኢንዱስትሪ የሚሸጋገሩ የፈጠራ ስራዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የኢኖቬሽንና ኢንኩቤሽን ማዕከልም የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ ያሉ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች ሀሳብ ወደስታርት አፕ ለመቀየር ብሎም ሀብት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በስኬት የተጠናቀቀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ ለማድረግ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራም ለምርምር ተቋማት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው፣ ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት አብርሃም ደበበ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሳይንስ ባህል ግንባታ ላይ ለዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
የስቴም ትምህርቶችን ከዚህ ቀደም ከዘጠነኛ ክፍል ይሰጥ እንደነበር ጠቅሰው፤ የሳይንስ ባህል ግንባታውን ወደታችኛው የትምህርት ደረጃ ለማስፋት በማሰብ በአሁኑ ወቅት ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች መካተታቸውን አስረድተዋል።
በቅርቡም የማህበረሰብ ትምህርት ቤት መክፈቱ ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ ተማሪዎች ሳይንስና ቴክኖሎጂን እንዲገነዘቡ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን የሳይንስ ሙዚየም ተማሪዎችን እንደላቦራቶሪ እገዛ እያደረገ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የዲጂታላይዜሽን ዘርፉን የሚመሩ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሰው ኃይል ልማት ላይ እየሰራ ነው ብለዋል።