ቀጥታ፡

ከፖለቲካ ስብራት ወደ ማንሰራራት

መስከረም 25/2019 (ኢዜአ)፡- ከፖለቲካ ስብራት ወደ ማንሰራራት

ትልቅ ሀገር- ትልቅ ህዝብ- ታላቅ ርእይ

ኢትዮጵያ ረጅም የፖለቲካ ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም፣ ይህ ታሪክ በተለያዩ ወቅቶች በፖለቲካዊ መገለል፣ በአለመተማመን፣ በአለመግባባትና በግጭት የተቆራረጠ መንገድ አልፏል። የፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ የሀገሪቱ ህዝቦች፣ ክልሎችና የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በእኩልነት እንዲሳተፉ የሚያስችል ምህዳር ለመፍጠርም ብዙ ፈተናዎች አልፈዋል።

ከብዙ ልፋት በኋላ በሀገሪቷ የመጣው ለውጥ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት፣ ምህዳሩን በማስፋትና ልዩነቶችን በሃሳብ ክርክር ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ አውድ ፈጥሯል። ይህም ከቆየው የፖለቲካ ስብራት ወደ ማንሰራራት የሚወስድ መልካም እድሎችን ይዞ የመጣ ሆኗል። 

ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የፖለቲካ ተሳትፎ በመስፋቱ የፖለቲካ አውዱ የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙበት ማድረግ አስችሏል። የሀገር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት እንዲሆን የሚያስችል የፖለቲካ አውድ መፈጠር አስችሏል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተወሰኑ ክልሎች “አጋር” እየተባሉ በሀገራቸው ጉዳይ እንዳይወስኑ እና እኩል ተሳታፊ እንዳይሆኑ ተገድበው ቆይተዋል። አሁን ላይ ግን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል ተሳትፎና ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በዴሞክራሲ ሥርዓት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሚና መንግሥትን መቃወም ብቻ አይደለም። አማራጭ ፖሊሲዎችን ማቅረብ፣ ለህዝብ የተሻለ አማራጭ ማቅረብና በሀገር ጉዳይ ላይ ገንቢ ሚና መጫወትም ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ ባለፉት ጥቂት አመታት በሃሳብ የበላይነት የሚመራና ክርክር የሚደረግበት እድል መኖሩ በተግባር ታይቷል። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በመንግሥት አመራር ውስጥ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ተቋማትን የመምራትና ህዝብን የማገልገል ዕድል ማግኘት ችለዋል።

በአንድ ሀገር ውስጥ የፓርቲዎች እንዲሁም የመንግስት መምጣትና መሄድ የማይቀርና የተለመደ ነው፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ግን ከግለሰቦችና ከፓርቲዎች በላይ ቆመው ለህግ፣ ለፍትሕና ለህዝብ ጥቅም መስራት አለባቸው። በመሆኑም በኢትዮጵያ መሰረቶች በመጠናከራቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ማድረግ የታቸለበት እድል ተፈጥሯል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር እድገትና የሀገረ መንግስት ግንባታ በአንድ ፓርቲ ወይም በአንድ መንግሥት ብቻ የሚጠናቀቅ አይደለም። የሁሉም ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የክልሎች፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም