ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል? - ኢዜአ አማርኛ
ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል?
ትልቅ ሀገር- ትልቅ ህዝብ- ታላቅ ርእይ
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በሀገሪቷ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን የማስቀጠል፤ በተለይም የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለስኬት ማብቃት ትልቁ የቤት ስራ ነው የሚሆነው።
በከተሞች እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማትና የስማርት ሲቲ ግንባታ፣ የዲጂታል አገልግሎቶችን የማስፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ማስቀጠል ሌላኛው ሀገራዊ ሃላፊነት ነው የሚሆነው።
የኢትዮጵያ ልማት በከተሞች ጋር ብቻ የሚወሰን ባለመሆኑ በገጠር አካባቢዎች የተጀመሩ የገጠር ትራንስፎርሜሽን የልማት ስራዎችንም ማስቀጠል የግድ ይላል። የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዋነኛ ዓላማም የገጠሩን ህዝብ አኗኗር ማዘመን፣ የመሠረተ ልማትና የመሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽነትን ማሻሻል፣ የገጠር ኢኮኖሚን ማጠናከርና የገጠር ነዋሪዎችን ከዘመናዊ የምርትና የገበያ ሥርዓት ጋር ማስተሳሰር መሆን አለበት።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በባህልና በሃይማኖት የበለፀገች ሀገር በመሆኗ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መፍጠር፣ ያሉትን የመጠበቅና የማልማት እንዲሁም ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን መጠበቅ፣ የቱሪስት ቆይታን ማራዘምና ከቱሪዝም ጋር የተሳሰሩ የስራ እድሎችን የማስፋት ጉዳይ የአዲሱ መንግስት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል።
በግብርናው ዘርፍም በምርትና ምርታማነት፣ በመስኖ ልማት፣ በስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በቡና፣ በሆርቲካልቸርና በሌሎችም የግብርና ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎች በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ማድረግ ይጠበቃል። ከምርት መጨመር ባሻገር የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር፣ የገበያ ትስስርን ማሻሻል፣ የማከማቻና የመጓጓዣ ስርዓትን ማዘመን እና የአርሶ አደሩን ገቢ የማሳደግ ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል።
የምርትና ምርታማነት መጨመር በመጨረሻም ከውጭ የሚገቡ የምግብ ምርቶችን በመተካት፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አቅም በማሳደግ ከተረጅነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ማሳካት ይጠበቅበታል።
የማዕድን ልማት፣ ዲጂታላይዜሽንና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ጉዳይም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል።
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የምርትና የገበያ አቅርቦትን ማሳደግ፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን ማሻሻል፣ ህገወጥ የገበያ አሰራሮችን መቆጣጠርና የዜጎችን የመግዛት አቅም ማሻሻል ይጠበቃል። የኑሮ ውድነት ችግር በአንድ መፍትሄ የሚፈታ ባለመሆኑ የገቢ፣ የምርት፣ የገበያና የፋይናንስ ፖሊሲዎችን በተቀናጀ መልኩ ማስኬድ ያስፈልጋል።