የአካታች ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ፅኑ መሰረት - ኢዜአ አማርኛ
የአካታች ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ፅኑ መሰረት
መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):- አዲሱ የመንግስት ምስረታ - አካታች የፖለቲካ ስርአት ግንባታ መሰረት
ትልቅ ሀገር- ትልቅ ህዝብ- ታላቅ ርእይ
በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ መንግስት የመመስረት ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ በዛሬው እለት ይሄው የሚከናወን ይሆናል።
በፓርላማው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መቀመጫ ያገኙ በመሆኑ የፖለቲካ ክርክሮችና የሃሳብ ብዝሃነት የሚስተናገዱበት እንደሚሆንም ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ስርአት ግንባታ መሰረት ያኖረው አዲሱ የመንግስት ምስረታ ሂደት የክልሎች ተጠናቆ በዛሬው እለት የፌዴራል መንግስት ምስረታ እውን ይሆናል።
ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው የአካታችነት ስኬት የመንግሥት ከፍተኛ የአመራር እርከኖች፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የፍትህ ተቋማት አመራሮች ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮችን፣ የሴቶችንና የወጣቶችን ፍትሃዊ ስብጥር በተግባር ማሳየት ያስቻለ ነው። ከባለፉት አምስት አመታት ተሞክሮ በመነሳትም የዘንድሮው ምርጫ በብዙ መስፈርቶች ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና አካታች መሆኑን በተግባር ያሳየና የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ፅኑ መሰረት ያኖረ ሆኗል።
በተቋማዊ አካታችነትና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በተወሰዱ እርምጃዎችም ጉልህ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ሁሉንም የፖለቲካና የኅብረተሰብ ክፍሎች ያቀፈው ሀገራዊ የምክክር ሂደት በሀገሪቷ የቆዩ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት አዲስ ምእራፍ የከፈተ ሆኗል።
ከዚህ ጎን ለጎን የጽንሰ-ሐሳብ፣ የቋንቋና የባህል ስብጥሮችን ያከበሩ የትምህርትና የባህል ፖሊሲዎች መተግበራቸው፣ ዜጎች በቋንቋቸው የመማርና አገልግሎት የማግኘት መብታቸው እንዲሰፋ በማድረግ ረገድም ትልቅ ስኬት ታይቷል።
በመሆኑም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው የብልፅግና ፓርቲ የሚያቋቁመው አዲሱ መንግስት በቀጣይ ሁለንተናዊ አካታችነትን በማረጋገጥ ረገድ ብዙ እንደሚሰራ ይጠበቃል።
ገዢው ፓርቲ መወዳደር የሚችልባቸውን አካባቢዎች በመተው ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እድሉን መስጠቱ በምክር ቤቱ የተለያዩ ድምፆች እንዲስተጋቡ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ሆኗል። በመሆኑም ጠቅላላ ምርጫው የፖለቲካ ተሳታፊነትንና ውክልናን በማስፋት ረገድ ጉልህ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነበር ማለት ይቻላል።
በተጨማሪም በውሳኔ ሰጪነትና በፖለቲካ ውድድር ውስጥ የሴቶች፣ የወጣቶችና የልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እንዲያድግ በመደረጉ ህዝባዊ ወካይነት ያለው የምርጫ ሂደትን ለማከናወን አስችሏል።
ምርጫ አስተዳደሩንና አሰራሩን አሳታፊና ፍትሃዊ በማድረግ ረገድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል የታዩት እርምጃዎች ሌላው የአካታችነት ማሳያዎች ናቸው።
የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ተዳራሽ ማድረግ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ የምርጫ ግብዓቶችን ማዘጋጀት እና በምርጫ ታዛቢነት የሲቪክ ማህበራትን፣ የሀገር ውስጥና የውጪ ምርጫ ታዛቢዎችን ማሳተፍ ተችሏል። ይህም የህብረተሰቡ ልዩ ልዩ ክፍሎች ያለምንም ገደብ የመምረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙና በሂደቱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጎለብት አድርጓል።
በመሆኑም በዛሬው እለት የሚመሰረተው መንግሥት ልዩ ልዩ የፖለቲካና የማህበረሰብ ክፍሎችን ድምፅ በማስተናገድና ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት የሚያኖር እንደሚሆን ይጠበቃል።