ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት-የብሔራዊ ጥቅም ዘብ

ኢትዮጵያ ዛሬ አዲስ መንግሥት ትመሠርታለች።ይህ መንግሥት የዛሬውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን፤የመጪውንም ትውልድ ፍላጎት በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆም ሥራ የሚሠራ ነው። አዲሱ መንግሥት ትልቅ የሕዝብ አደራ የሚቀበልና የነገዋን ኢትዮጵያ በከፍታ ላይ የሚያስቀምጥ እንደሚሆን እሙን ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ ውስብስብ የሆኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፈተናዎች አልፋ ዛሬ አዲስ የምዕራፍ ላይ ትገኛለች። አዲሱ መንግስት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን፣ ሉዓላዊነቷን እና የሕዝቦቿን የጋራ እድገት ለማረጋገጥ ባደረገችው ያላሰለሰ ጥረት ውስጥ ቀጣይ ጉዞዋን በተሻለ መልኩ የሚያስቀጥል መንግሥት ይሆናል።

ይህ ታሪካዊ ጉዞ በቀላሉ የተገኘ አልነበረም። ሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን በቃላት ሳይሆን በተግባር ለመወሰን፣ መብቱን በድምፁ በመጠቀም ታሪካዊ አደራውን ለመወጣት ውስብስብ ፈተናዎችን አልፏል። በፈተና ውስጥ አልፎ የሰጠው ድምፅ ተራ የምርጫ ሂደት ሳይሆን፤ የሀገርን ሕልውና የማስከበር፣የብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ እና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር የማስረከብ ጽኑ ፍላጎት መግለጫ ነበር።

ዛሬ የሚመሠረተው አዲስ መንግሥት የዚሁ የሕዝብ አደራና የጽናት ውጤት ነው።ይህ የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ቀጣናዊ ጥቅሞች ያስከብራል፤ የኢትዮጵያን የሉዓላዊ ድንበር እና የወደፊት ሕልውና በጠንካራ ዲፕሎማሲና በውስጥ አንድነት ይጠብቃል። የዛሬዎቹን አጣዳፊ ጥያቄዎች ለመመለስ ብቻ ሳይሆን፣ መጪው ትውልድ የሚተማመንባት፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች እና ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስጠብቅ ሀገር መንግስት ይመሰርታል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሁለት ውኃዎች ላይ አድርጋ በጽናት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። የአባይን ውኃ ለሁለንተናዊ እድገቷ መጠቀም ጀምራለች፤ ሕዳሴንም ጨርሳ የማድረግ አቅሟን አረጋግጣለች።ይህ ጉዞ ቀላል አልነበረም፤ሀገሪቱ በውስጥና በውጭ በርካታ ፈተናዎችን፣ ተፅዕኖዎችንና ጫናዎችን አልፋ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የበለጠ የሚያስከብርላትን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ አንሥታ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ አጀንዳ አድርጋዋለች። የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሐዊና ባልተገባ መልኩ ያጣችውን የባሕር በሯን እንድታገኝ በትክክለኛው መንገድ ይጓዛል፤ ግቡንም ያሳካል።

ዛሬ የሚመሠረተው አዲስ መንግሥት ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መደላደል የሚፈጥር ነው፤ የሀገሪቱን የባሕር በር ፍላጎት፣የዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣የውስጥ ደኅንነትና የኢኮኖሚ ነፃነት አፅንኦት ሰጥቶ ማስጠበቅ ነው።ልዩነቶችን በማቀናጀትና አቅሞችን በመደመር የሀገርን ሕልውና አስተማማኝ ማድረግም ሌላው ከመደመር መንግስት የሚጠበቅ ነው።

ከምንም በላይ ኢትዮጵያ የበርካታ ዘመናት ታሪካዊ ጠላቶቿንና ተላላኪዎቻቸውን እኩይ ሴራ ትበጣጥሳለች።የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በህዝቦቿ ጽናት፣የአንድነት መንፈስና የማይናወጥ ሀገራዊ ወኔ እያሸነፈች ትቀጥላለች።ለነፃነቷና ሉዓላዊነቷ ሳትበገር በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ወደ ላቀ የልማት፣ የብልፅግናና የዕድገት ከፍታ ወደ ፊት መገስገሷን ትቀጥላለች።

ዛሬ የሚመሰረተው አዲሱ የመደመር መንግሥትም የሕዝቡን ተስፋና እምነት ወደ መሬት በማውረድ፣የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አክብሮና አስከብሮ ለመጪው ትውልድ የምትመችና በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባች ሀገርን የማስረከብ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም