ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ

መስከረም 25/2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ

ትልቅ ሀገር- ትልቅ ህዝብ- ታላቅ ርእይ

የዛሬው እለት ኢትዮጵያ በፖለቲካዊ ታሪኳ ሌላ አዲስ ምዕራፍ የምትከፍትበት ታሪካዊ እለት ነው። በግንቦት ወር የተካሄደው ምርጫ፣ የሕዝብ ድምፅና ውሳኔ ወደ ተጨባጭ የመንግሥት ምስረታ የተሸጋገረበት ወቅት ላይ ይገኛል።

የሕዝብ ድምፅ ድምር ውጤት መንግስት የሚመሰረትበትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ጽኑ መሰረት የያዘበት አዲስ የታሪክ ምእራፍ ተከፍቷል።

የምርጫ ሂደት በራሱ የሚጠናቀቀው የምርጫ ውጤት በመገለጹ ብቻ ባለመሆኑ የሕዝብ ውሳኔ በተቋማት በኩል ተግባራዊ ሲሆንና የሕዝብን የልማትና የአገልግሎት ፍላጎት ማስተናገድና ምላሽ መስጠት የሚችል መንግስት ሲመሰረት ነው። በዚሁ መሰረትም ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ክልሎች የመንግሥት ምስረታ ሂደታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል።

በዛሬው እለት ደግሞ የፌዴራል መንግስት የሚመሰረትበት፤ አዲሱ ፓርላማ ሥራውን በይፋ የሚጀምርበትና አዲስ የፌዴራል መንግሥት የሚመሠረትበት ታሪካዊ እለት ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶችንና የለውጥ ወቅቶችን አሳልፋለች። በእያንዳንዱ ዘመን የሀገሪቱ ፖለቲካ በሕዝቡ ፍላጎት፣ በሀገራዊ ጥቅምና በዘመኑ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ሥር ወድቆ የታየበት አጋጣሚ የበዛ ነበር ማለት ይቻላል። የዛሬው የመንግስት ምስረታ ግን ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምፃቸውን በነፃነት የሰጡበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ድምር ውጤት ነው።

በመሆኑም አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የቆዩ የፖለቲካ ስብራቶችን በማከም የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚተልምና ቀጣይ መዳረሻዋን የሚወስን ይሆናል። 

ታላቋን ኢትዮጵያ ለመምራት ትልቅ ርዕይ የሰነቀ መንግስት የግድ በመሆኑ እንደ ሀገር የተያዙ እቅዶችን በተደመረ አቅም በማሳካት እድገትና ማንሰራራቷን ማስቀጠል ይገባል። በመሆኑም አዲሱ መንግሥት በምርጫ ወቅት ለህዝብ የገባውን ቃል በማክበር ለተግባራዊነቱ መትጋት ይጠበቅበታል። የህዝብን አደራ በአግባቡ በመወጣት ቃልን በተግባር መፈፀም የግድ ይላል። የዜጎች የሥራ ዕድል፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ፣ የልማት ፍላጎት፣ የፍትሕ አገልግሎትና የመንግሥት ተጠያቂነት የአዲሱ መንግስት የቤት ስራዎች ናቸው።

ፓርላማውም ሕግ ከማውጣት ባሻገር የመንግሥትን አፈጻጸም መከታተል፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥና የዜጎችን ድምፅ ወደ ፖሊሲና የሕግ አቅጣጫ መቀየር ይጠበቅበታል። በዚህ መልኩ የሚቀጥለው ፓርላማ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን በማጠናከር የህዝብ የልማት መሰረቶች ተጠናክረው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሰራ ይሆናል።

የሕዝብ ድምፅ የሥልጣን ምንጭና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት የሚያኖር መሆኑ ይታወቃል። በህዝብ ድምጽ የተሰጠ ሃላፊነት ደግሞ ተጠያቂነት ጭምር ያለበት አደራ ነው። በመሆኑም አዲሱ መንግስት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለዘላቂ ሰላምና ልማት፣ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታና የህግ የበላይነት መስራት ይጠበቅበታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም