የኢትዮጵያ የፅናት ጉዞ እና የካይሮ የጥፋት እጆች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የፅናት ጉዞ እና የካይሮ የጥፋት እጆች
ታሪክ ደጋግሞ እንደሚያስተምረን፤ የኢትዮጵያ ልማት፣ እድገት እና በቀጣናው ላይ የሚኖራት አዎንታዊ ተፅዕኖ ማደግ በካይሮ የፖለቲካ ሊሂቃን ዘንድ እንደ ስጋት ሲቆጠር ኖሯል።የዓባይን ውሃ በብቸኝነት የመቆጣጠር የቆየ ስትራቴጂ የምትከተለው ግብፅ፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም እና በኢኮኖሚ ጠንካራ ሀገር ሆና እንዳትወጣ ለማድረግ ያልፈነቀለችው ድንጋይ፣ ያልተጠቀመችበት የጂኦፖለቲካዊ ሴራ አልነበረም።
ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያን በውስጥ ባንዳዎች እና ቅጥረኞች በፋይናንስና በመሳሪያ በመደገፍ ሀገሪቱን ለማዳከም የተሄደባቸው መንገዶች በሙሉ በኢትዮጵያውያን አይበገሬነት እና በሉዓላዊነት ላይ ባላቸው የማይናወጥ ጽናት ምክንያት መና ቀርተዋል። በቅርቡ ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና ወደ ሥራ መግባት፣ ያንን የቆየውን የቅኝ ግዛት ውል እና "እኔ ብቻ ልጠቀም" የሚለውን አግላይ እሳቤ ላይመለስ አክሽፎታል።
በቀጥታ ወታደራዊ ግጭት ወይም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ኢትዮጵያን ማንበርከክ ያልቻለችው ካይሮ፣ አሁን ላይ የስልት ለውጥ በማድረግ የውክልና ጦርነት ስትራቴጂን በሰፊው ማካሄድ ጀምራለች። ለዚህ እኩይ አላማዋ ደግሞ በአስመራ የሚገኘውን የሻዕቢያ አስተዳደር እንደ ፈጻሚ አካል መጠቀም ከጀመረች ሰነባብታለች።
ሁለቱን ወገኖች ያገናኛቸው የጋራ ፍላጎት ልማት ወይም የህዝቦች እድገት ሳይሆን፤ "ኢትዮጵያን የማዳከም፣ የማተራመስ እና በቀጣናው አቅም አልባ የማድረግ" እኩይ ግብ ነው። የዚህ ያልተቀደሰ ጋብቻ ዋና ስትራቴጂ፡ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በውስጥ ግጭትና አለመረጋጋት እንድትጠመድ ማድረግ። ሀገሪቱ ትኩረቷን እና ሀብቷን ወደ ጸጥታ ማስከበር እንድታዞር በማድረግ በታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያላትን አቅም ማዳከም።የሀገሪቱን የመከላከል አቅም ለመበታተን በተለያዩ አቅጣጫዎች የጸጥታ ስጋት መፍጠር ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ይህ ጣልቃ ገብነት በግልጽ በሚታይ ደረጃ ላይ ደርሷል። የኤርትራ ሠራዊት የውስጥ ታጣቂዎችን በመደገፍ፣ በቀጥታ በጦርነት በመሳተፍ የጸጥታ ስጋት በመፍጠር እና የፌደራል መንግሥቱን ለማዳከም እየሰራ ይገኛል። ይህም ግብፅ በስተጀርባ ሆና በገንዘብ፣ በመሳሪያ እና በዲፕሎማሲ የምታግዘው ግልጽ የውክልና ጦርነት አካል ነው።
ነገር ግን ታለቋ ኢትዮጵያ የሉዓላዊነቷን ወሰን እና የብሔራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ሴራዎች በዝምታ እንደማትመለከት በተግባር እያሳየች ትገኛለች። የውስጥ ሰላሟን ከመጠበቅ ጎን ለጎን፣ የውጭ ኃይላትን ድብቅ ሴራ የሚያከሽፉ ጠንካራ የዲፕሎማሲ እና የመከላከል እርምጃዎችንም ወስዳለች።
በብሔራዊ ደህንነት ላይ አደጋ በሚደቅኑ ተግባራት ላይ በቀጥታ የተሳተፉ 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከሀገር እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ በአስመራ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲም ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ ተደርጓል።በተመሳሳይ ሁኔታ ከግብፅ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና ድብቅ ጣልቃ ገብነት በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ አንድ የግብፅ ዲፕሎማት ሀገር ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ጠንካራ መልዕክት አዘል ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።
ከዲፕሎማሲያዊ ውሳኔዎቹ ባሻገር፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የገቡትን እና በካይሮ እና በአስመራ የተላኩትን የሻዕቢያ ወታደራዊ ኃይሎች እንዲሁም የውስጥ ቅጥረኞችን የማጽዳት ስራንም በተሳካ ሁኔታ እያከናወነች ትገኛለች።
ኢትዮጵያን በታሪክ አጋጣሚ ሁሉ በቀጥታ ወታደራዊ ወራራ ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋ ያልተሳካላት ግብጽ አስመራን እየላከች የሄደችበት የሴራ ቀመር ዛሬ ላይ መንቀሳቀስ የሚችል አይደለም። ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ አይደለችም። የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ የውስጥ ድክመቷን ተደግፎ የፈለጉትን ሴራ የሚያስኬዱባት ደካማ ሀገር አይደለችም።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የናይልን የውሃ ፖለቲካ የበላይነት በቋሚነት ቀይሮታል። ሀገሪቱ በቀጣናው የኢነርጂ እና የኢኮኖሚ ማዕከል ሆና ብቅ ብላለች።የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዘመናዊ የውጊያና የቴክኖሎጂ አቅም በመታጠቅ የሀገርን ሉዓላዊነት በጽኑ መደብ ላይ ገንብቷል፤ ማንኛውንም የውስጥና የውጭ ስጋት በከፍተኛ አቅም የመመከት፤ ሲያስፈልግም የማጥቃት ሙሉ ብቃት አለው።
በመሆኑም ካይሮ እና አስመራ በጋራ የሸረቡት የማተራመስና የውክልና ጦርነት ሴራ የዛሬዋን ኢትዮጵያ አዲስ እውነታና ቁርጠኝነት ባላገናዘበ ስሁት ስልት ላይ የተመሠረተ ነው።
ቀደም ሲል በታሪክ አጋጣሚዎች በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ጠላቶች የተጎነጎኑ ጥምረቶች ሁሉ በኢትዮጵያውያን አይበገሬነት መና እንደቀሩት ሁሉ፣ አሁንም በካይሮ ታቅዶ በአስመራ የሚፈጸመው እኩይ ድራማ የታሰበበት ግብ ሳይደርስ በጽኑ የኢትዮጵያ ክንድ የሚከሽፍ እና የትም የማይደርስ መሆኑ የማይቀር ሀቅ ነው።