ከፈተናዎች ማዶ የተቀናጀ ድል፡የኢትዮጵያ ጽናትና የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
ከፈተናዎች ማዶ የተቀናጀ ድል፡የኢትዮጵያ ጽናትና የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ምዕራፍ
ኢትዮጵያ የታሪክ፣የሥልጣኔ፣ የጽናትና የነፃነት ምልክት የሆነች የታላቅ ሕዝብና የታላቅ ርዕይ ሀገር ናት።ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ያስመዘገበቻቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ድሎች በቀላሉ የተገኙ ሳይሆን፣ በውስጥና በውጭ ያሉ የቀጣናው የጥፋት ኃይሎች የሰነዘሩባትን ሁለገብ ተፅዕኖና ሴራ በጽናት በመመከት የተረጋገጡ ናቸው።
የክልልና የፌዴራል ምክር ቤቶች አደረጃጀት ተጠናቆ የኢፌዴሪ አዲስ መንግሥት የሚመሠረትበት ይህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያዊነትን ጠንካራ መሠረት፣ የሕዝቡን የዴሞክራሲ ምርጫና የሀገሪቱን ታላቅ ርዕይ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ ያበሰረ አጋጣሚ ነው።
ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ልማት፣ ለጋራ እድገትና ለሰላም ጠንክራ በቆመች ቁጥር፣ የሀገሪቱን እድገትና ጥንካሬ እንደ ስጋት የሚያዩ ኃይሎች እንቅፋት ለመሆን ከመስራት ተቆጥበው አያውቁም።
ከካይሮ የሚጠነሰሱና በቀጣናው ባለው የሻዕቢያ ቡድንና በተላላኪዎቹ በኩል የሚፈጸሙ የጥፋት ዕቅዶች የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ለማላላትና የማልማት አቅሟን ለማሰናከል የተዘረጉ ናቸው።
የግብጽ ገዥዎች ቀደም ብሎ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ግንባታና አጠቃቀም ለማደናቀፍ በየዓለም አቀፉ መድረክ ከግንባታው ጀምሮ እያደረጉት ካሉት ከመርህ ያፈነገጠ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ባሻገር፣ የቀጣናውን አለመረጋጋት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮጵያ ትኩረቷን እንድትበትን ሰፊ ሴራ ሲሸርቡ ቆይተዋል።
የሻዕቢያ ቡድን ደግሞ የካይሮ አዛዦቹን ሥራ ለመፈጸም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ ፅንፈኛ የጥፋት ቡድኖችን በማስታጠቅ፣ በማሰልጠንና በፋይናንስ በመደገፍ ኢትዮጵያን የማዳከም ስትራቴጂ ሲከተል ቆይቷል።
እራሱ ምንም ዓይነት የምርጫና የዴሞክራሲ ታሪክ የሌለውና ሕዝቡን ያለ ምርጫ በኃይል የሚገዛው የሻዕቢያ ቡድን፣በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማደናቀፍ፣ በድንበር አካባቢዎችና በውስጥ በሚንቀሳቀሱ ባንዳዎች በኩል ከንቱ ሙከራ አድርጓል።
የኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ጽናት፡ "ያለ ምርጫ ሀገር አትቀናም"
በተለያዩ አካባቢዎች የተደቀኑት ስጋቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ የምርጫ ካርዱን ከመጠቀም አላገዱትም። ኢትዮጵያውያን በነቃና በተደራጀ ሁኔታ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሄድ ድምፃቸውን ከንጋት እስከ እኩለ ሌሊት ተሰልፈው ሰጥተዋል።
ሕዝቡ በስጋት ውስጥም ቢሆን ለፈተናዎች ሳይበገር "ያለ ምርጫ ሀገር አትጸናም፣ መንግሥትም አይቆምም" በማለት በነቂስ ወጥቶ መምረጡ ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱና ለሀገሩ ያለውን ጽኑ አቋም ለወዳጅም ለጠላትም አሳይቷል።በምርጫው ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት የመሠረተ ቢሆንም፣ በርካታ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በክልል ምክር ቤቶችና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ቀላል የማይባሉ መቀመጫዎችን ማሸነፋቸው የሕዝቡን ድምፅ ስብጥርነት የሚያሳይና የዴሞክራሲ ልምምዱን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ነው።
የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ሂደት
የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ምክር ቤቶች በስኬት ተቋቁመዋል። የክልል መንግሥታትና አስተዳደሮች አዲስ አመራሮቻቸውን በመሰየም ሥራ ጀምረዋል።
የፌዴራል መንግሥት ምሥረታና የአዲስ ካቢኔ ማጽደቅ ተግባርም ከነገ ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ ይከናወናል። ይህ ሂደት ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት፣ በሕዝብ ፈቃድና በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የምትመራ ዘላቂና ጠንካራ ሀገር መሆኗን ማረጋገጫ ነው።
አዲሱ መንግሥት የውስጥ ልማቱንና ብልጽግናውን ከማረጋገጥ ባሻገር ለቀጣናውና ለአፍሪካ አህጉር የሚከተሉትን ታላላቅ ርዕዮች ይዞ ይሰለፋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማስቀጠል፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማፋጠን እንዲሁም የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ከዋና ዋና ሥራዎቹ መካከል እንደሚሆኑ ይታመናል።
በምሥራቅ አፍሪካ ግጭቶችን በዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ማሳደግ ብሎም ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የአፍሪካ ህብረት አጀንዳዎችን ከፊት ሆኖ የማስፈጸምና የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ የማሰማት ሚና በተጠናከረ መንገድ ለመወጣት የሚሰራ ይሆናል።
በካይሮና በሻዕቢያ የሚሰነዘሩት የቀጣናዊ ልማት ጠንቆችና የጥፋት ዕቅዶች የቱንም ያህል ቢወሳሰቡ፣የኢትዮጵያን የሥልጣኔና የብልጽግና ጉዞ ማቆም አይችሉም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው ያሳየው ብስለትና የሀገር ፍቅር፣ የጥፋት ኃይሎችን ዕቅድ ያከሸፈና አዲሱን መንግሥት በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ላይ የተከለ መሆኑን በሚገባ አሳይቷል።
ኢትዮጵያ በነገው ዕለት የምትመሠርተው አዲስ መንግሥት የሕዝቧን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጥ፣ የቀጣናውን ሰላም የሚያስከብርና ለአፍሪካ ሕዳሴ ከፊት የሚሰለፍ የታላቅ ሀገርና የታላቅ ሕዝብ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።