ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው የኢንዱስትሪ ማዕከልነት የጎላ አስተዋጽኦ አለው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለዘላቂ ኢኮኖሚ፣ ለቀልጣፋ የሎጂስቲክስ አገልግሎትና ለቀጣናው የኢንዱስትሪ ማዕከልነት የጎላ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዘመዴነህ ንጋቱ ገለጹ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዘመዴነህ ንጋቱ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ የራሷ የባህር በር ባለመኖሩ በየዓመቱ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ ላይ ከ40 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች ብለዋል፡፡

የዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (የአይ.ኤም.ኤፍ) ጥናት ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛዋ ፈጣን ኢኮኖሚ ያስመዘገበች መሆኗን የሚያመለክት ቢሆንም፣ ይህንን እድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል የትራንስፖርት፣ ሎጂስቲክስና የወደብ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

አገሪቷ ግዙፍ የህዝብ ቁጥር፣ ትልቅ የኢኮኖሚ መጠን፣ እምቅ ሀብቶችና ሰፊ የሀገር ውስጥ ገበያ ያላት መሆኗን አመልክተው፤ የባህር በር ችግሯ ከተቃለለ የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ማዕከል መሆን እንደምትችል ገልጸዋል። 

ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙት የኮቪድ-19፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም የጂኦፖሊቲክስ ቀውሶች የዓለምን ኢኮኖሚ መፈተናቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቋሚነት ማደጉ ጠንካራና ተቋቋሚ ኢኮኖሚ መገንባቱን በአይ ኤም ኤፍና በዓለም ባንክ መረጃዎች መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ 

ለዚህ ስኬት የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ፣ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግና የተቋማት ሪፎርም ያካተተው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል። 

በተለይም በፖሊሲ ማሻሻያዎች ምክንያት የወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር ያደገ ሲሆን፤ ይህም በአጋጣሚ ሳይሆን በትኩረት በተሰራ ስራ የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቡና በተጨማሪም የወርቅ ምርት ለውጡን በግንባር ቀደምትነት ማሻሻሉን ጠቅሰዋል፡፡ 

በአጠቃላይ አሰራርንና ፖሊሲዎችን ማሻሻል እንዲሁም የወጪ ንግድ ምርቶችን ዓይነት ማበራከት ለቀጣይ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂነት ወሳኝ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡  

የካፒታል ገበያ መቋቋሙ ዜጎች በየቀኑ አክሲዮን እንዲገዙና ኩባንያዎች ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ማስቻሉን እንዲሁም በቴክኖሎጂ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝምና ግብርና ዘርፎች አገራዊ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ድርጅት (UNCTAD) ሪፖርትን መሠረት በማድረግ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በቋሚነት ከአፍሪካ አምስቱ ትልልቅ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተቀባይ አገራት መካከል ስትሆን፤ ይህም ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤት እንደሆነ አመልክተዋል። 

የቢሾፍቱ አየር መንገድ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካና የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ግዙፍ ልማቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

አገሪቱ ያላትን የኢኮኖሚ ሳቢነት ዘላቂ ለማድረግና ኢንቨስትመንት መሳቧን ለመቀጠል፣ ተቋማቶቿን ማጠናከር፣ አዳዲስ አሰራሮችን ይበልጥ መዘርጋት እንዳለባት ጠቅሰዋል፡፡ 

በቀጣይ በአዲሱ መንግስት ምስረታ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ አዳዲስ ኢንሼቲቮችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም