ሻዕቢያ - ሰላም ቀውሱ፤ ጦርነት ምሱ - ኢዜአ አማርኛ
ሻዕቢያ - ሰላም ቀውሱ፤ ጦርነት ምሱ
ገና ከምሥረታው ጀምሮ ርዕዮቱ ክፋት፣ የስራ ውጤቱ ጥፋት ነው። ለኤርትራና ህዝቦቿ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ሳያመጣ ግማሽ ክፍለ ዘመናትን ተሻግሯል። በሀገሩ መንግስት እንደመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት ከሰራው ይልቅ በጎረቤት ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ሲፈተፍት የኖረው ይበልጣል። የፈጸማቸው እኩይ ተግባራት፤ ሰላምን ለማወክ የሄደበት ርቀት የማንነቱ ህያው ማሳያዎች ናቸው። ጥፋት መገለጫው ነው። ከዚያም በላይ በቀጣናው የግብፅን የጥፋት ተልዕኮ በማስፈጸምና በመፈጸም ግንባር ቀደም ነው - ሻዕቢያ።
የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ነኝ በሚል የዳቦ ስም እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1970 የተመሰረተው ሻዕቢያ አመሰራረቱም በተንኮል የተሞላ ነበር። ሻዕቢያ ከጀብሃ የተገነጠሉ ነፃ አውጭ የሚያስፈልጋቸው "የነፃነት ታጋዮች ነን" የሚሉ የኢሳያስ አፈወርቂ ጀሌዎች ስብሰብ ውጤት ነው። የኢሳያስ የግል የጥፋት ኢንተርፕራይዝ።
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካ ዘርፎች ትስስር መፍጠር ለሚያስችሉ ጉዳዮች ትኩረት ትሰጣለች፤ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት በሚለው የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ አቅጣጫዋ በጋራ መልማት፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በልማት መተሳሰር ትፈልጋለች። በኢኮኖሚ ልማት የቀጣናው መሪም ሆናለች።
የቀጣናው ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በጋራና በተናጠል ዘርግታለች፤ ዛሬም አልቦዘነችም። ይሄውም ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላም እና ልማት መቼም የማይነጥፍ ፍላጎት እና አቋም እንዳላት ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ የማደግ ጽኑ ፍላጎት፤ ከምትከተለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ይመነጫል፤ ቀጣናውን አስተሳሳሪ መሰረተ ልማቶችን ገንብታለች፤ በሂደት ላይ ያሉም አሉ፤ ቀጣይነትም ይኖረዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያቀርበው የኤሌክትሪክ ሀይል ታንዛኒያ ይደርሳል፤ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ ሀይል ይቀርብላቸዋል። የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙም አሉ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ…።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በሕዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት፣ በጋራ የመልማት አቅም፣ ፍላጎት እና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግስት ዕሳቤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በወንድማማችነት መርህ እንዲሆን በመሻት በሕወሓትና ሻዕቢያ እብሪት ለሩብ ክፍለ ዘመን ተቋርጦ የነበረውን የሁለቱን ሀገራት ህዝብ ዳግም እንዲገናኝ አድርገዋል።
የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ እና በባህል፤ በሀይማኖታዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲጠናከር ኢትዮጵያ ብዙ ርቀት እንድትጓዝ አድርገዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ጥረቱም ፍሬ አፍርቶ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ዳግም ተበስሯል። ኤርትራ ስትማቅቅበት የነበረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው ደፋር የፖለቲካ ውሳኔ፣ ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነትና የጋራ ዕድገት የሚበጅ አዲስ መንገድ መክፈት ያስቻለ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ባውጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ታሪካዊ እና ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ታከብራለች፤ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቁርጠኛ ናት ብሏል።
ኤርትራ ምንም እንኳን ለልማትና ዕድገት የሚተጋ መሪ ባትታደልም ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ተፈጥሮ በነበረው ሰላማዊና መልካም ጉርብትና የኤርትራ ህዝብ የልማት ጭላንጭት እንዲያይ አድርጓል፤ የነፋስ ላይ ኩራዝ ሆነ እንጂ።
ኢትዮጵያ በሻዕቢያና ሕወሓት አውዳሚ የፖለቲካ መስመር የነበረውን የፖለቲካ ስንጥቃት በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አድርጋለች፤ ይሄውም የምስራቅ አፍሪካን ቀጣናዊ ውህደትና ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ መሠረት የጣለ ነበር። ይህን ታሪካዊ ግንኙነት በፖለቲካ ሳይወሰን በህዝቦች መካከል ባለው ጠንካራ ማህበራዊና ባህላዊ ቁርኝት ላይ የተደገፈ ነበር። ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር አስተማማኝ ሰላምና የጋራ ብልፅግና የማረጋገጥ ፍላጎት ጭምር። ግን ምን ዋጋ አለው “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” ሆነና ነገሩ የጥፋት ጠንሳሹ ኢሳያስ ሰላም ባላጋራው ነውና ተደናቀፈ።
ሻዕቢያ ከምስረታው ጀምሮ ሌሎችን የማጥፋት የፖለቲካ አካሄድ ይከተላል። በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የጥፋት ሀይሎችን መፈልፈል፣ መደግፍ ግብሩ፤ ዜጎቹን ማፈን፣ የልማትና የሰላም ጥያቄ ማንሳትን እንደ ወንጀል ማየት ደግሞ ህልውናው ነው።
ሻዕቢያ የጥፋት መሪው ኢሳያስ አፈወርቂ ስሪትና ውጤት ነው፤ ኢሳያስ ልማትን አሻግሮ የሚያይ ወይም የሚያቅድ አዕምሮ የለውም። ሻዕቢያ ለውጥና ልማትን በሩቁ በሚሸሸው አምባገነኑ ኢሳይያስ አስተሳሰብ የተቃኘ በመሆኑ ለሀገሪቱ የቁልቁለት ጉዞ ዛሬም ሽምጥ ይጋልባል።
ኢትዮጵያ ሻዕቢያ ከዕኩይ ተግባራቱ በመታቀብ በጋራ መበልጸግ በሚያስችሉ የልማት ስራዎች ላይ እንዲያተኩር ብዙ ለፍታለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽኦ የዓለም የሰላም ኖቤል ሎሬት ሽልማት አግኝተዋል፤ ይህ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ዋጋና ቁርጠኝነት ዓለም እንዲረዳ አድርጓል።
ሻዕቢያ የተጣባውን ቀጣናውን የመበጥበጥ ድርጊት ዛሬም ቀጥሎበታል። በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሕወሓትና ሌሎች ጽንፈኛ ሀይሎችን በስንቅና ትጥቅ በመደገፍ ቀጣናውን ለሁከት ይጋብዛል። ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፈጸም በኢትዮጵያ በአምሳሉ የፈጠራቸውን የውስጥ ባንዳዎች የዕኩይ ዓላማው ማስፈጸሚያ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነትና ቀጣናዊ ውህደትን አጥበቃ ትሻለች። በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ትንኮሳ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጠይቃለች። በኢትዮጵያ ጠንካራ እምነት መሠረት የቀጣናው እውነተኛ ጠላት "ድህነት" ነው። ለዚህ ደግሞ መድሃኒቱ በጋራ መልማትና ማደግ ነው። ለዚህም ነው ለጋራ ልማት ተግታ የምትሰራው።
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የሚደረግ የሰላም ትብብር ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሁለቱ ሀገራት የሰላምና የልማት ትብብር ወሳኝ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚናገሩት።
ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር ተግታ ትሰራለች። ይህንንም በተግባር አሳይታለች። በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የተሳለጠ ማህበራዊና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር፣ የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲያደግ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች።
ሻዕቢያ መሰረቱ የሕዝብ ፍላጎት ባለመሆኑ ዛሬም ጥፋት ያውጃል። የግብጽን ተልዕኮ ለመፈጸም ከአስመራ ካይሮ በመመላለስ አጀንዳ በመቀበልና በማስፈጸም ከኢትዮጵያ አልፎም ቀጣናውን ለማተራመስ ይተጋል።
የሻዕቢያ አሰራር ዴሞክራሲያዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ፣ በውስጥ በኩል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ የዜጎችን መሰረታዊ ነጻነቶች መገደብ እና ስልጣንን በኃይል ላይ ብቻ በመመስረት ለዓመታት መቆጣጠርን የተከተለ ነው። የሕዝብ ድጋፍ የሌለው ይህ አገዛዝ ሁል ጊዜም ትኩረትን ከውስጣዊ ችግሮች ለማሸሽ የውጭ ጠላት ያለ ማስመሰልን እንዲሁም ቀጣናዊ አለመረጋጋት በመፍጠር ዘመኑን ለማራዘም የሚተጋ እኩይ ድርጅት ነው።
የሻዕቢያ አስተዳደር ከግብጽ እና ከሌሎች የውጭ ኃይሎች ጋር ያለው ግንኙነት ቀጣናውን ማበጣበጥ ላይ ያተኮረ መሆኑ በግልጽ ይስተዋላል። የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ ወደ ካይሮ በመመላለስ ቀጣናዊ ሚዛንን ለመቀየርና የኢትዮጵያን የልማትና የሰላም እንቅስቃሴዎች ለማደናቀፍ የሚደረጉ የጋራ እኩይ ተግባራት ማሳያ ናቸው። ለግብጽ ኢትዮጵያ ተዳክማ ማየት ሕልሟ ነው። ሻዕቢያ ደግሞ በመላላክ ለመፈጸም የቆመ የራሱ አሮበት የሌላውን የሚያምስ ለሕዝቡም ፋይዳ ያለው ነገር የማይፈጽም የቀጣናው ሰላም የሚያቃዠው ነው። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት ለመቀናቀን ከውጭ ሃይሎች የሚሰጡ ትዕዛዞችን መቀበልና መተግበር የቡድኑ ዋና ስልት ሆኖ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገው ይገኛል። የሰሞኑ እንቅስቃሴ የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው።
የቀጣናው መረጋጋት እጦት ዋነኛ ምንጭ የሆኑ ድርጊቶች ከዚሁ ጠባብ አመለካከት ከተጠናወተው የግብጽ ተልዕኮ ፈጻሚው ሻዕቢያ ሃይል የሚመነጩ ናቸው። የኢትዮጵያን ሰላም ማደፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናውን በዘላቂ ግጭት ውስጥ ለማቆየት የሚደረጉ ርብርቦች በቀጣናው ደህንነት ላይ አደጋ ይፈጥራል።
ሻዕቢያ ህገ ወጡ ሕወሃትን በመደገፍ ዛሬም ቀጣናውን ለማተራመስ በሚደረጉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች፣ ታጣቂ ቡድኖችን በማሰልጠን፣ በገንዘብና በሎጂስቲክስ በመደገፍ በኩል የውጭ ሃይል የሆነው የላኪው እጆች እንዳሉበት መረጃዎች የሚያረጋግጡት ጉዳይ ነው።
ሻዕቢያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በንግድ፣ በኢኮኖሚ በመተሳሰር በሰላም መኖር የማይችልበት ዋናው ምክንያት፣ ሰላም ከሰፈነ አምባገነናዊ ስርዓቱ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባና ተጠያቂ እንደሚደረግ ስለሚያውቅ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። የኤርትራን ህዝብ ግማሹን በመግደል፣ ግማሹን በወህኒ ቤት ያለፍርድ በማጎር፣ ግማሹን ለስደት በመዳረግ ቀሪውን ደግሞ ለግዳጅ ወታደራዊ ስልጠና በማስገባት አምባገነን ቡድን መሆኑ በተግባር ያረጋገጠ የቀጠናው አሸባሪ ቡድን ነው። ሻዕቢያ ሀገሪቱን የምድር ሲዖል አድርጓታል።
በርግጥ የሻዕቢያ አምባገነን ቡድን በገዛ ዜጎቹ እየተነሱ ያለው የሰላም፣ የዲሞክራሲ እና የልማት ጥያቄዎች እየገፉ በመምጣታቸው ድንጋጤ ውስጥ ገብቷል። ከዚህ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ለመሸሽ እና በአጀንዳ ለመጥመድ በማሰብ ኢትዮጵያንና ቀጣናውን ማተራመስ የመጀመሪያው ተግባሩ አድርጓል። ለዚህ ተግባሩ በግብፅ እግር ስር ወድቆ ይላላካል። ይህ እኩይ ተግባሩ ቀጣናውን ሁል ጊዜም በውጥረት ውስጥ ማቆየት ለህልውናው ዋስትና አድርጎ መውሰዱን ያሳያል።
የዴሞክራሲ ሀሁ የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለዜጎቹ የነፈገው የሻዕቢያ ኢ-ዴሞክራሲየዊ አገዛዝ ቀጣናውን የማተራመስና የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ የማስፈጸም የተላላኪነት አካሄድ ከጊዜ ወደ ጊዜ አደገኛ መልክ እየያዘ መምጣቱ በግልጽ ተስተውሏል። ይህንን አጥፊ አካሄድ ለመግታት የምስራቅ አፍሪካ የቀጣናው ሀገራት ጉዳዩን ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት ሊመለከቱትና ጥልቅ ትንተና ሊሰጡበት ይገባል፡፡
የቀጣናው ሀገራት የሻዕቢያ ሴራ ማብቂያ የለውም ብለው ማመን እና አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሰላም ሲደፍርስ ዝም ማለት ወይም ችላ ማለት፣ ቀስ በቀስ ቀውሱ ወደ ሌሎቹም ሀገራት እንደሚደርስ ተገንዝቦ አቋም መያዝ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ግብጽን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች በቀጣናው ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሻዕቢያን እንደ መነሻና የጦር ሜዳ በመጠቀም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቀጣናውን ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አለመረጋጋት ውስጥ ሊከተው ስለሚችል፣ ጉዳዩን እንደ የጋራ የህልውና ስጋት ማየት ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ አሁን ነው።
የቀጣናው መንግስታት ከሻዕቢያ እና ከደጋፊዎቹ የሚሰነዘሩ ድብቅ አጀንዳዎችንና የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመከታተል ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዘርጋት ይገባቸዋል።
የውጭ ኃይሎች የቀጣናውን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት እንዳይፈጽሙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ማክሸፍ ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው።