ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የባዕዳንን ተልዕኮ የሚያስፈጽም ተላላኪ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የባዕዳንን ተልዕኮ የሚያስፈጽም ተላላኪ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2019 (ኢዜአ)፦ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የባዕዳንን ተልዕኮ የሚያስፈጽም ተላላኪ ነው ሲሉ ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ፡፡
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
በዚህም ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሱ ለሥልጣን ጥቅም ሲል እስከ መጨረሻው ድረስ ክህደትና ጥፋት ከመፈጸም እንደማይመለስ በተደጋጋሚ አሳይቷል ብለዋል።
ቡድኑ ለውጥ የሚፈልግና ልዩ ሃሳብ የሚያነሳን ማንኛውንም አካል በማግለልና በማጥፋት እስከ አሁን ድረስ ለራሱ የሚሆነውን ብቻ ሲያመቻች መቆየቱንም አብራርተዋል።
አሁን ወደዚህ ሁሉ ጦርነትና ቀውስ የገባው በራሱ የተሳሳተ የፖለቲካ ትንተና እና የላኪዎቹን ተልዕኮ በመቀበል እነርሱን ለማስደሰት እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል።
ግጭቱ በየት፣ እንዴትና መቼ መጀመር እንዳለበት የመወሰን ፈቃደኝነትም ሆነ ሥልጣን በቡድኑ እጅ ሳይሆን በሚልከው አካል እጅ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ የባዕዳን አዛዦችን ትእዛዝ በመቀበል የባዕዳንን ሥራ እንዲሠራ ተልዕኮ የወሰደ መሆኑን አንስተው፤ እንደ አስፈጻሚ አካል የተባለውን ብቻ የሚያደርግ ተላላኪ መሆኑንም አብራርተዋል።
የሀገሪቷ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ ጠንካራና አቅም ያላት ሀገር እንድትሆን የማይፈልጉ ሀገራት መኖራቸውን አንስተው፣ ይህ የጽምዶ ጥምረት የዚሁ አካል ሥራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ዋና ፍላጎታቸው ሀገሪቷ ሁል ጊዜም በትርምስ እና በሁከት እንድትኖር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ተረጋግታና ሰላሟ ጸንቶ ወደ ትላልቅ ስትራቴጂካዊ አጀንዳዎቿ እንዳትሸጋገር ቀን ከሌሊት ሁሌም በተለያየ መንገድ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
አካላቱ ይህን አጀንዳቸውን ለማሳካት ይፋዊ የሆኑ ግጭቶችንና ጥምረቶችን ከመፍጠር ባለፈ፤ በእምነትና በትምህርት ዘርፎች በኩል ሳይቀር በተለያዩ መንገዶች እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።
በአፋቸው ሌላ እያሉ በተግባር ግን የሀገሪቷን አንድነት ለማዳከም አስተሳሰብን ለመበተንና ሀገርን ለማፍረስ የተዘጋጀውን አጀንዳ የሚያስፈጽም የውስጥ ሽፍታ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አብራርተዋል።